19 ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በብራስልስ የዳይመንድ ሊግ ፍፃሜ ላይ ይሳተፋሉ
DL Trophy - Photo by Matthew Quine
የ2024 የዳይመንድ ሊግ የፍፃሜ ውድድር ዓርብ እና ቅዳሜ (መስከረም 3 እና 4/2017 ዓ.ም.) በቤልጂየም ብራስልስ ይካሄዳል፡፡ በሁለቱም ፆታዎች 19 ኢትዮጵያውያን (7 ወንዶች እና 12 ሴቶች) አትሌቶች በአራት የውድድር አይነቶች ለዓመቱ የዳይመንድ ሊግ አጠቃላይ አሸናፊነት በሚደረጉ የፍፃሜ ፉክክሮች ላይ ይሳተፋሉ፡፡
በ5000 ሜትር እና በ3000 ሜትር መሰናክል በሁለቱም ፆታዎች እንዲሁም በሴቶች 800 ሜትር እና 1500 ሜትር ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በብራስልስ የሚፎካከሩባቸው ርቀቶች ናቸው፡፡ በዓመቱ የዳይመንድ ሊግ ውድድሮች ላይ ባስመዘገቡት ነጥብ መሰረት ለብራስልሱ የፍፃሜ ፉክክር ማለፋቸውን አረጋግጠው ከነበሩት ኢትዮጵያውያን አትሌቶች መካከል የሴቶች 3000 ሜትር መሰናክል ተወዳዳሪዋ ሲምቦ አለማየሁ በቪዛ ችግር ምክንያት ቀርታለች፡፡ የአውሮፓ ህብረት ምክር ቤት ለኢትዮጵያ ዜጎች በሚሰጠው የሸንገን ቪዛ አገልግሎት ላይ በኤፕሪል መጨረሻ ላይ የጣላቸው ገደቦች ለውድድር ወደተለያዩ የአውሮፓ ሕብረት አባል ሀገራት በሚሄዱ አትሌቶች የቪዛ ፕሮሰስ ላይ እንቅፋት እየፈጠረ ይገኛል። አሁን ለኢትዮጵያውያን የሚሰጠው ሸንገን ቪዛ የነጠላ መግቢያ ብቻ ሲሆን የማመልከቻ ፕሮሰሱ የሚወስደው ግዜም ከ15 ወደ 45 ቀን ከፍ እንዲል ተደርጓል፡፡ ይህም በተለይም በትራክ ውድድር ላይ በተቀራራቢ ግዜ ለሚወዳደሩ አትሌቶች እጅግ አስቸጋሪ ፈተና ሆኗል።
በወንዶች 5000 ሜትር ሰለሞን ባረጋ እና አዲሱ ይሁኔ፣ በወንዶች 3000 ሜትር መሰናክል ለሜቻ ግርማ፣ እንዲሁም በሴቶች 5000 ሜትር ልቅና አምባው በነበራቸው ነጥብ ለዳይመንድ ሊግ ፍፃሜ ተፎካካሪነቱ አልፈው የነበሩ ቢሆንም ባልተገለፁ ምክንያቶች በፍፃሜው ውድድር ላይ አይገኙም፡፡
በኪንግ በድዊን ስታዲየም በየዓመቱ የሚካሄደው የሜሞሪያል ቫን ዳም የአትሌቲክስ ውድድር ዘንድሮ የዋንዳ ዳይመንድ ሊግ የሁለት ቀን የፍፃሜ ውድድሮችን ያስተናግዳል፡፡ የዳይመንድ ሊግ ፍፃሜ ውድድሮች ወደዚህ ስታድየም ዘንድሮ ሲመለሱ ከ2019 ዓ.ም. በኋላ ለመጀመሪያ ግዜ ነው፡፡ በፓሪስ ኦሊምፒክ ላይ አሸናፊ የሆኑ 18 አትሌቶችም የሚሳተፉበትን የሁለቱ ቀናት ውድድሮች ከ70,000 በላይ ደጋፊዎች እንደሚታደሙት ይጠበቃል፡፡ በብራስል የዓመቱ የዳይመንድ ሊግ የአጠቃላይ አሸናፊ ለሚሆኑ አትሌቶች 30,000 ዶላር እና የዳይመንድ ዋንጫ በሽልማትነት ይበረከታል፡፡ የዘንድሮው ዳይመንድ ሊግ ፍፃሜ አሸናፊዎች በቀጣዩ የዓለም ሻምፒዮና ላይ የቀጥታ ተሳታፊነት ዕድል አያገኙም፡፡ የ2025 ዳይመንድ ሊግ ፍፃሜ ከቶኪዮ ዓለም ሻምፒዮና በፊት የሚከናወን በመሆኑ የቶኪዮ ዓለም ሻምፒዮና የቀጥታ ተሳታፊነት ዕድል (Wild Card) ለ2025 ዳይመንድ ሊግ አሸናፊዎች የሚሰጥ ይሆናል።
በ2024 የዋንዳ ዳይመንድ ሊግ ብራስልስ ላይ በሚደረጉት የፍፃሜ ውድድሮች አሸናፊ ለሚሆኑ አትሌቶች የሚበረከተው የገንዘብ ሽልማት ዝርዝር:-

ዓርብ እና ቅዳሜ በብራስልስ ዳይመንድ ሊግ ውድድር ላይ የሚሳተፉት ኢትዮጵያውያን አትሌቶች የውድድር ፕሮግራም:-

