January 15, 2026

በታለሀሲ ማርታ በግል ወርቅ ስታሸንፍ፣ በሪሁ እና ሰናይት የቡድን የወርቅ ድሉን መርተዋል

በታለሀሲ ፍሎሪዳ በተካሄደው 46ኛው የአለም ሀገር አቋራጭ ሻምፒዮና የ20 አመት በታች ቡድኑን የቪዛ ችግር ተጨማሪ ሜዳልያዎችን ከማግኘት ቢገድበውም ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ጥሩ ውጤቶችን አስመዝግበዋል።

አዋቂ ወንዶችበሪሁ አረጋዊ በተከታታይ ለሶተኛ ግዜ የብር ሜዳልያ ያስገኘበት

በአዋቂ ወንዶች ፉክክሩ ኡጋንዳዊው ጃኮብ ኪፕሊሞ (28፡18) ለሶስተኛ ተከታታይ ጊዜ የአለም አገር አቋራጭ ሻምፒዮን ሆኗል፡፡ ኢትዮጵያዊው በሪሁ አረጋዊም (28፡36) በሻምፒዮናው ላይ በተከታታይ ለሶስተኛ ግዜ ሁለተኛ ወጥቶ የብር ሜዳልያ በመውሰድ አጠናቋል። ይህ ድል ለበሪሁ በትልልቅ ዓለም አቀፍ ውድድር ላይ ያስመዘገበው አምስተኛው የብር ሜዳሊያ አሸናፊነት ስኬት ሆኖም ተመዝግቦለታል። ምንም እንኳን በግሉ የወርቅ ሜዳልያ ለማሸነፍ የነበረው ግብ ባይሳካም በሪሁ በብር ሜዳልያ ድሉ የኢትዮጵያን ቡድን በመምራት ለወርቅ ሜዳልያ ድል አብቅቷል።

ለኢትዮጵያ ቡድን የአዋቂ ወንዶች የወርቅ ሜዳልያ ድል ነጥብ ያስመዘገቡት አራት አትሌቶች፡-

በሪሁ አረጋዊ – 2ኛ (የብር ሜዳልያ አሸናፊ)

ታደሰ ወርቁ – 4ኛ (ከ2 ዓመት በፊት በቤልግሬድ የጨረሰበትን 12ኛ ደረጃ በማሻሻል)

ቢንያም መሐሪ – 6ኛ

ንብረት ክንዴ – 18ኛ

አራቱ አትሌቶች ይዘው ያጠናቀቁት ደረጃ ሲደመር ያስገኘው 30 ነጥብ ከኬንያ (34) እና ዩጋንዳ (39) በመላቅ የኢትዮጵያ ቡድን የወርቅ ሜዳልያ አሸናፊ እንዲሆን አስችሏል፡፡ በዚህ ውድድር ላይ ኢትዮጵያን ከወከሉት ስድስት አትሌቶች መካ

ከል ከነበሩት በረከት ነጋ 35ኛ ደረጃን ይዞ ሲያጠናቅቅ መዝገቡ ስሜ ውድድሩን ለማቋረጥ ተገዷል።

በግሉ የብር ሜዳልያ ያገኘው በሪሁ ከውድድሩ በኋላ በሰጠው አስተያየት ‹‹ፉክክሩ በጣም ከባድ ነበር፡፡ የተዘጋጀሁት ወርቅ ሜዳልያ ለማሸነፍ ቢሆንም የብር ሜዳልያ ማግኘቴም ጥሩ ነገር ነው፡፡ ኡጋንዳዊው ጃኮብ ኪፕሊሞ በተከታታይ ለሶስተኛ ግዜ ለማሸነፍ የበቃ በጣም ጠንካራ አትሌት ነው፡፡ ያው ውድድር እስከሆነ ድረስ ባገኘሁት ውጤት ደስተኛ ነኝ፡፡›› ብሏል፡፡

አዋቂ ሴቶች – ሰናይት ጌታቸው ለኢትዮጵያ የነሐስ ሜዳልያ ያስገኘችበት

የውድድሩን የቅድሚያ የአሸናፊነት ግምት አግኝታ የነበረችው ኬንያዊቷ አግነስ ንጌቲች (31፡28) እንደተጠበቀችው ውድድሩን በመቆጣጠር የወርቅ ሜዳልያው አሸናፊ ስትሆን ኢትዮጵያ የቡድን የበላይነቱን ወስዳለች፡፡

ኢትዮጵያዊቷ ሰናይት ጌታቸው ከኡጋንዳዊቷ ጆይ ቼፕቶዬክ ጋር የብር ሜዳልያ አሸናፊ ለመሆን ከባድ ፉክክር ስታደርግ ነበር፡፡ ቼፕቶዬክ  በመጨረሻው ዙር መሰናክሎቹ ጋር በተሻለ አፈፃፀም ወደ ፊት በማለፍ 32፡10 በሆነ ሰዓት የብር ሜዳልያውን አሸንፋለች፡፡ የሰናይት ጌታቸው (32፡13) የነሐስ ሜዳልያ ድል በሌሎቹ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ጠንካራ ስራ ታግዞ የቡድን ወርቅ ሜዳልያን አስገኝቷል።

ለኢትዮጵያ ቡድን የአዋቂ ሴቶች የወርቅ ሜዳልያ ድል ነጥብ ያስመዘገቡት አራት አትሌቶች፡-

ሰናይት ጌታቸው – 3ኛ (ነሐስ)

አሳየች አይቼው – 4ኛ

አለሺኝ ባወቀ – 5ኛ

አለም ፃዲቅ – 7ኛ

አራቱ አትሌቶች በጨረሱባቸው ደረጃዎች ድምር 19 ነጥብ ኢትዮጵያ 36 ነጥብ ካስመዘገበችው ኬንያን እና 37 ነጥብ ካገኘችው ኡጋንዳ ልቃ የቡድን ፉክክሩን የወርቅ ሜዳሊያ ለማሸነፍ ችላለች፡፡ በዚህ ውድድር ላይ ኢትዮጵያን ከወከሉ ስድስት አትሌቶች መካከል የነበሩ ሹሬ ደምሴ (33፡33) እና ለምለም ንብረት (34፡27) በቅደም ተከተል 12ኛ እና 26ኛ ደረጃን ይዘው አጠናቀዋል።

ከሶስት አመት በፊት በአውስትራሊያ ባትረስት የ20 ዓመት በታች የወርቅ ሜዳሊያ አሸናፊ የሆነችው ሰናይት፣ የታለሀሲ መወዳደሪያ ስፍራ በንፅፅር ባትረስቱ የበለጠ ፈታኝ እንደነበረ ጠቅሳ ‹‹መጀመሪያ ላይ ኬንያዊቷ አግነስ ንጌቲችን ለመከታተል ሞክሬያለሁ ነገር ግን እሷ ከአቅሜ በላይ ነበረች፡፡ ስለዚህ ቀሪዎቹን ተወዳዳሪዎች መቆጣጠሩ ላይ አተኩሬ ስሮጥ ነበር። እስከ መጨረሻው ጥቂት ሜትሮች ድረስም ለብር ሜዳልያው እየተፎካከርኩ ነበር፡፡ ሆኖም በመጨረሻው ዙር መሰናክሉ አካባቢ እግሬ ላይ የመደንዘዝ ስሜት ሲፈጠር ኡጋንዳዊቷ አትሌት ልትቀድመኝ ችላለች። በግሌ ባገኘሁት የነሐስ ሜዳያ ደስተኛ ነኝ፡፡ በቡድን የወርቅ ሜዳልያ በማሸነፋችንም በጣም ተደስቻለሁ›› ብላለች፡፡


20 ዓመት በታች ሴቶች – ማርታ አለማየሁ ከ20 አመት በታች ሻምፒዮንነቷን ክብር ያስጠበቀችበት

ኢትዮጵያዊቷ ማርታ አለማየሁ 18፡52 በሆነ ሰዓት ከሁለት ዓመት በፊት ያገኘችውን የሻምፒዮንነት ክብሯን ያስጠበቀ ድል ተቀዳጅታለች፡፡ ውድድሩን ከመጀመሪያ እስከ መጨረሻው በመምራት ድል ያደረገችው ማርታ በውድድሩ ታሪክ የሻምፒዮንነት ክብሯን ያስጠበቀች 4ኛዋ እንስት አትሌት ለመሆንም በቅታለች። ከኡጋንዳዊቷ ቻሪቲ ቼሮፕ ጋር ያደረገችውን ጠንካራ ፍልሚያ በበላይነት ያጠናቀቀችው ሌላኛዋ ኢትዮጵያዊት ወሰኔ አሰፋ 19፡18 በሆነ ሰዓት የብር ሜዳልያ ስታሸንፍ ቼሮፕ ከወሰኔ በአንድ ሰከንድ ባነሰ 19፡19 ሰዓት የነሐስ ሜዳልያ ወስዳለች።

የኢትዮጵያውያን አትሌቶች ውጤት:-
ማርታ አለማየሁ – 1ኛ (ወርቅ)
ወሰኔ አሰፋ – 2ኛ (ብር)
የኔነሽ ሽመክት (19፡35) – 5ኛ

በዚህ ውድድር ላይ የተሳተፉት ኢትዮያውያን አትሌቶች ምንም እንኳ በግል በጣም ጥሩ ውጤቶችን ቢያስመዘግቡም የቡድን ነጥብ አስቆጣሪ አንድ አትሌት የጎደላቸው መሆኑ ተጨማሪ ሜዳልያ ከማግኘት አግዷቸዋል፡፡ ይህ የሆነበት ምክንያትም ለዚህ ውድድር ተመርጠው ሲዘጋጁ የቆዩ አትሌቶች ቪዛ መከልከላቸው ነው። በቡድን ፉክክሩ ኡጋንዳ እና ኬንያ ዕኩል 29 ነጥብ በማመዝገብ በቅደም ተከተል የወርቅ እና ብር ሜዳልያ ሲወስዱ የጃፓን ቡድን የነሐስ ሜዳልያ አግኝቷል። ኡጋንዳ የቡድን ወርቅ አሸናፊ የሆነችው ‹‹ሁለት ቡድኖች ዕኩል ነጥብ ሲያስመዘግቡ የመጨረሻዎቹን ነጥብ አስቆጣሪ አትሌቶች ደረጃ በማነፃፀር የቀደመው አሸናፊ ይሆናል›› በሚለው የመለያ ሕግ መሰረት ነው።

20 ዓመት በታች ወንዶች – ብቸኛው ኢትዮጵያዊ ተሳታፊ 12 ሆኖ አጠናቋል
በ20 አመት በታች የወንዶች ውድድር ላይ ኢትዮጵያ በብቸኛው አትሌት አየለ ሰውነት የተወከለች ሲሆን ውድድሩን 24፡14 በሆነ ሰዓት 12ኛ ሆኖ አጠናቋል። አየለ ከውድድሩ በኋላ ከቡድን አጋሮች ውጪ ያደረገው ውድድር ስለነበረው ስነ ልቦናዊ ተፅእኖ ሲገልፅ ‹‹የቡድን አጋሮቼ ከእኔ ጋር ቢሆኑ ኖሮ የታክቲክ ድጋፍ እና የሞራል ጥንካሬ ይሰጡኝ ነበር›› ብሏል።

4×2 ኪሜ ድብልቅ ዱላ ቅብብል – ኢትዮጵያ የነሐስ ሜዳልያ ያገኘችበት

የታለሀሲው ውድድር መክፈቻ በነበረው የድብልቅ ዱላ ቅብብል ውድድር በወገኔ አዲሱ፣ ገላ ሀምበሴ፣ ሚልኬሳ ፍቃዱ፣ እና ሂሩት መሸሻ የተወከለችው ኢትዮጵያ የነሐስ ሜዳልያ ድልን አሳክታለች፡፡ በ2017 ዓ.ም. በኡጋንዳ ካምፓላ ከተጀመረ አንስቶ ሶስት የብር እና አንድ የወርቅ ሜዳልያ ስኬት ሪኮርድ ያላት ኢትዮጵያ በታለሀሲ ነሐስ ጨምራበታለች፡፡ በዚህ ውድድር ላይ ብርቱ ሯጮቿን ያሰለፈችው አውስትራሊያ የወርቅ ሜዳልያውን ስታሸንፍ፣ ፈረንሳይ የብር ሜዳልያ ወስዳለች። ኬንያ አራተኛ ሆና አጠናቃለች።
Photos © BizuAthletics.com (Bizuayehu Wagaw)