July 28, 2026

ኢትዮያዊቷ ሹሬ ደምሴ በቶሮንቶ ዋተርፍሮንት ማራቶን ሶስተኛ ድሏን አሳካች

Shure Demise 2025 TCS Toronto Waterfront Marathon Women's winner Photo by Carole Fuchs

እ.አ.አ ዕሁድ ኦክቶበር 19 ቀን 2025 ዓ.ም. ለ36ኛ ግዜ በተከናወነው የቲሲኤስ ቶሮንቶ ዋተርፍሮንት ማራቶን ከዘጠኝ ዓመት በኋላ የተመለሰችው ኢትዮጵያዊቷ ሹሬ ደምሴ የሴቶች ማራቶን ሶስተኛ ድሏን ተቀዳጅታለች፡፡ በወንዶቹ የማራቶን ፉክክር የኬንያ አትሌቶች የሜዳሊያ ደረጃዎቹ የበላይ ሆነው አጠናቀዋል።

የሴቶቹ ውድድር በ2015 እና 2016 የውድድሩ ሻምፒዮን የነበረችው ሹሬ ደምሴ ከዘጠኝ ዓመታት በኋላ ወደ ቶሮንቶ ተመልሳ ሶስተኛ ድሏን ያሳካችበት ሆኖ ተጠናቋል፡፡ ውድድሩን ከመጀመርያው ጀምሮ በልበ ሙሉነት ስትመራ የቆየችው ሹሬ ከውድድሩ አጋማሽ በኋላ ከተከታዮቿ ጋር የነበራትን ልዩነት በማስፋት ከውድድር ስፍራው ሪኮርድ በሀያ ሰከንዶች ከግል ምርጥ ሰዓቷ ደግሞ በአምስት ሰከንዶች ብቻ በራቀ 2፡21፡04 ሰዓት አሸንፋለች። የቶሮንቶ ዋተርፍሮንት ማራቶን የሴቶች ሪኮርድ ያለፈው ዓመት አሸናፊ በሆነችው የሀገሯ ልጅ ዋጋነሽ መካሻ የተመዘገበው 2፡20፡44 መሆኑ ይታወሳል፡፡ ኬንያዊቷ ቤቲ ቼፕኮሪር (2፡23፡46) እና ኢትዮጵያዊቷ አልማዝ ከበበ (2፡26፡41) በቅደም ተከተል ሁለተኛ እና ሶስተኛ በመሆን ጨርሰዋል፡፡ በዚህ ውድድር ላይ ተሳታፊ ከነበሩት ሰባት ኢትዮጵያውያን ውድድሩን ማጠናቀቅ የቻሉት ሁለቱ (ሹሬ እና አልማዝ) ብቻ ናቸው፡፡ ሶስት አትሌቶች (ጎጃም እንየው፣ ድባቤ በየነ፣ እና ንግስቱ ሀፍቱ) መሰመር በመሳት ከውድድሩ ውጭ ሲሆኑ አስማረች ነጋ እና አዳነ አንማው ደግሞ አቋርጠው ለመውጣት ተገደዋል፡፡

Winner
Shure Demise 2025 TCS Toronto Waterfront Marathon Women’s winner,  Photo by Carole Fuchs

የውድድሩ አሸናፊ የሆነችው ሹሬ ደምሴ ከድሏ በኋላ በሰጠችው አስተያየት ‹‹የልጅ እናት ሆኜ ከረጅም ግዜ በኋላ ወደቶሮንቶ መጥቼ ለሶስተኛ ግዜ አሸናፊ መሆን የቻልኩበትን ልዩ ውጤት በማስመዝገቤ በጣም ደስ ብሎኛል፡፡ በውድድሩ ላይ ከዚህ በፊት አስቸጋሪ ይሆን የነበረው ብርድ ያልነበረ ቢሆንም ንፋሱ ግን እጅግ ፈታኝ ነበር፡፡ ሆኖም የገጠመኝን ፈታኝ ንፋስ ተቋቁሜ ለአሸናፊነት በቅቻለሁ›› ብላለች፡፡

በሶስተኛ የማራቶን ውድድር ተሳትፎዋ ሶስተኛ ሆና ለማጠናቀቅ የበቃችው አልማዝ ከበበ ‹‹ሰዓቴን አሻሽላለሁ ብዬ ባስብም የነበረው ጠንካራ ንፋስ ወደፊት መግፋት አላስቻለኝም እናም ያገኘሁት ደረጃ ጥሩ ቢሆንም ሰዓቴ ግን ትንሽ ወደላይ ወጥቶብኛል›› ብላለች፡፡ አልማዝ በመጀመሪያዎቹ ሁለት የማራቶን ውድድር ተሳትፎዋ በተመሳሳይ ስምንተኛ ደረጃን ይዛ ነበር ያጠናቀቀችው፡፡

በወንዶቹ የማራቶን ውድድር ኬንያውያን አትሌቶች ሶስቱንም ሜዳልያዎች ጠራርገው ወስደዋል፡፡ ሊዮናርድ ላንጋት 2:08:05 በሆነ ሰዓት አንደኛ ሆኖ ሲያጠናቅቅ ኖሀ ኪፕኬምቦይ (2:08:29) እና ሲላ ኪፕቱ (2:08:46) በቅደም ተከተል ሁለተኛ እና ሶስተኛ ወጥተዋል፡፡

በኢትዮጵያ በኩል ከተሰለፉት ስምንት አትሌቶች ወርቅነህ ታደሰ (2:09:04) 4ኛ፣ ይሁንልኝ አዳነ (2:09:05) 5ኛ፣ በላይ ጥላሁን (2:10:12) 7ኛ፣ ደመቀ ተስፋዬ (2:10:46) 8ኛ፣ እና ዳኛቸው ማሩ (2:16:52) 11ኛ  ሆነው ጨርሰዋል፡፡ ያለፈው አመት ሻምፒዮን የነበረው ሙሉጌታ ኡማ፣ ምትኩ ጣፋ እና ድንቁ ካሳሁን ውድድሩን አቋርጠው ለመውጣት ተገደዋል።

የ2025 ቲሲኤስ ቶሮንቶ ዋተርፍሮንት ማራቶን በሙሉ እና ግማሽ ማራቶን ከ70 ሀገራት የተውጣጡ 22 ሺህ ተሳታፊዎች ነበሩት፡፡

በሴቶች ማራቶን ውድድሩ ላይ ሶስት ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ያጋጠማቸው አሳዛኝ ክስተት
በ36ኛው የቶሮንቶ ዋተርፍሮንት ማራቶን የሴቶች ውድድር ላይ ሶስት ኢትዮጵያውያን አትሌቶች አቅጣጫ መሳታቸው በብዙ ልፋት የተዘጋጁበትን ውድድር ውጤት በሚያሳዝን ሁኔታ አበላሽቶባቸዋል፡፡ ስህተቱ የተፈጠረው 20ኛው ኪሎ ሜትር አቅራቢያ የግማሽ ማራቶን እና ማራቶን ተሳታፊዎች ለሁለት የሚከፈሉበት ቦታ ላይ ሲሆን የማራቶን ተወዳዳሪዎቹ ወደ ግማሽ ማራቶን ተወዳዳሪዎች አቅጣጫ በመግባታቸው ነው፡፡ የተሳሳተውን አቅጣጫ ተከትለው ወደ ግማሽ ማራቶን መጨረሻው መስመር በመሄዳቸውም የማራቶን ውድድሩን መቀጠል ሳይችሉ ቀርተዋል። በዚህም ምክንያት የኢትዮጵያውያኑ ጎጃም እንየው እና ድባቤ በየነ ሩጫ ዲስኳፋይድ በመባል እና በልብ ስብራት ተጠናቋል። በተመሳሳይ የመሮጫ መስመር የሳተችው ንግስቲ ሃፍቱ ወደኋላ ለመመለስ እና ውድድሩን ለመቀጠል ሞክራ የነበረ ቢሆንም መጨረስ ሳትችል ቀርታለች።

20ኛው ኪሎ ሜትር አቅራቢያ የመሮጫ መስመሩ ለሁለት ሲከፈል የግማሽ ማራቶን ተሳታፊዎቹ ቤይ ስትሪትን ተከትለው ከናታን ፊሊፕስ ስኩዌር በስተምስራቅ እስከ መጨረሻው መስመር ድረስ ሲሄዱ የማራቶን ተወዳዳሪዎች ወደ ዌሊንግተን ጎዳና በመታጠፍ ወደ መሃል ከተማ ከመሄዳቸው በፊት ለብዙ ኪሎ ሜትሮች ወደ ምስራቅ አቅጣጫ መሮጥ ነበረባቸው። የወንዶቹን ውድድር በአሯሯጭነት ያግዝ የነበረው አትሌት ተወዳዳሪዎቹን አስከትሎ ወደተሳሳተው አቅጣጫ ሊገባ ሲል የግማሽ ማራቶን ውድድሩን ይመራ የነበረው አትሌት ትክክለኛውን የማራቶን መሮጫ መስመር ሲጠቁመው እንደነበር በቴሊቪዥን የቀጥታ ስርጭቱ ላይ ታይቷል፡፡ እንደ እድል ሆኖም የሴቶቹን ውድድር በአሯሯጭነት ያግዝ የነበረው አትሌት አሸናፊዋ ሹሬ ደምሴን እና ከሷ ኋላ ይከተሉ የነበሩት አትሌቶችን በትክክለኛው አቅጣጫ መርቷቸዋል፡፡

የውድድሩ አዘጋጆች በክብር እንግድነት የጋበዟቸው ሰዎች ድባቤ በየነ የግማሽ ማራቶን ውድድሩ አሸናፊ መስላቸው ለአሸናፊዎች የሚዘረጋውን ባነር ይዘው ሲጠብቋት በአትሌቷ እና በክብር እንግዶቹ ፊት ላይ የታየው ግራ መጋባትም ሌላኛው በቀጥታ ስርጭቱ የታየ የሚያሳዝን ክስተት ነበር፡፡ አትሌቶች የግማሽ ማራቶኑን መሮጫ መስመር እንዳይከተሉ በቅዳሜው የቴክኒክ ስብሰባ ላይ መመሪያ ተሰጥቷቸው የነበረ ቢሆንም፣ ለሚወዳደሩበት ከተማ እና ለውድድሩ እንግዳ ለሆኑ እንዲሁም የቋንቋ ውስንነት ላለባቸው አትሌቶች የዚህ አይነቱን ኃላፊነት መስጠት ትንሽ የበዛ ነው፡፡