በፖላንድ ቶሩን በተካሄደ የቤት ውስጥ ሩጫ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በመካከለኛና ረጅም ርቀት የበላይነታቸውን አሳይተዋል።
በፖላንድ ቶሩን በተካሄደው 10ኛው የኦርሊን ኮፐርኒከስ ካፕ የቤት ውስጥ ውድድር ኢትዮጵያውያን አትሌቶች የበላይ ሆነው አምሽተዋል፡፡ በወንዶች 1500 ሜትር ሳሙኤል ተፈራ፣ በወንዶች 3000 ሜትር ሰለሞን ባረጋ፣ በሴቶች 800 ሜትር ሀብታም ዓለሙ፣ በሴቶች 1500 ሜትር ፍሬወይኒ ሀይሉ አሸናፊ ሆነው ሲያጠናቅቁ በወንዶች 1500 ሜትር በሁለተኛነት ያጠናቀቀው ታዳጊው ቢኒያም መሀሪ የዓለም ከ20 ዓመት በታች ሪኮርድን አሻሽሏል፡፡
በወንዶች 1500 ሜትር የርቀቱ የሁለት ጊዜ የአለም የቤት ውስጥ ሻምፒዮን ሳሙኤል ተፈራ በመጨረሻዎቹ 100 ሜትሮች ውስጥ የአጨራረስ ልምዱን ተጠቅሞ በ3፡34.61 ሰዓት በአንደኛነት አጠናቋል፡፡ የዘንድሮ ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ 10 ኪሎ ሜትር ውድድር አሸናፊው ቢኒያም መሀሪ ሁለተኛ ሆኖ ባጠናቀቀበት የመጀመሪያ ዓለም አቀፍ የትራክ ውድድር ተሳትፎው 3፡34.83 በሆነ ሰአት ላለፉት አምስት ዓመታት በኖርዌያዊው ጃኮብ ኢንገብሪትሰን ተይዞ የቆየውን የአለም ከ20 በታች ክብረወሰን አሻሽሏል። የታዋቂው የቀድሞ የረጅም ርቀት ሯጭ ገብረእግዚአብሔር ገብረማሪያም የወንድም ልጅ የሆነው ቢኒያም በቶሩን ያስመዘገበው ሰዓት የወንዶች 1500 ሜትር የፓሪስ ኦሎምፒክ ሚኒማን ለማሟላት በጣም የቀረበ እና በ1.5 ሰከንድ ብቻ የዘገየ ነው።

በወንዶች 3000 ሜትር ሰለሞን ባረጋ የውድድር ስፍራውን ሪኮድ እና የራሱን ምርጥ ሰዓት ባሻሻለበት የወቅቱ ፈጣን ሰዓት 7:25.82 አንደኛ ሆኖ ጨርሷል፡፡ ሊጠናቀቅ ስድስት ዙር ሲቀረው አንስቶ የአሸናፊነቱ ፉክክር በሁለቱ ኢትዮጵያውያን ሰለሞን ባረጋ እና ጌትነት ዋለ መካከል ነበረ፡፡ ነገር ግን ሁለት ዙር ሲቀር ጌትነት ፍጥነቱን ጠብቆ ሊከተለው ባለመቻሉ የወቅቱ የርቀቱ የዓለም የቤት ውስጥ ሻምፒዮኑ ሰለሞን የመሪነት ግስጋሴውን አጠናክሮ በመቀጠል አሸንፏል፡፡ የዓመቱ የግል ምርጥ በሆነ 7:26.73 ሰዓት በሁለተኛነት ያጠናቀቀው ጌትነት ዋለ በሁለት ውድድሮች ተሳትፎው ባስመዘገበው 14 ነጥብ ለ2024 ወርልድ ኢንዶር ቱር አጠቃላይ አሸናፊነት የሚደረገውን ፉክክር መምራት ጀምሯል፡፡ ነጥብ በሚመዘገብባቸው ውድድሮች የአጠቃላይ አሸናፊ ሆነው የሚያጠናቅቁ አትሌቶች በቀጣዩ ወር በስኮትላንድ ግላስጎው በሚካሄደው የዓለም አትሌቲክስ የቤት ውስጥ ሻምፒዮና በቀጥታ ተሳታፊ የሚሆኑበትን ዕድል ያገኛሉ፡፡ በቶሩኑ የወንዶች 3000 ሜትር ውድድር ላይ ተሳታፊ የነበረው ሌላኛው ኢትዮጵያዉ አዲሱ ግርማ 8:03.35 በሆነ ሰዓት አራተኛ ወጥቷል፡፡
በሴቶች 800 ሜትር ሀብታም ዓለሙ በቤት ውስጥ ውድድር ለመጀመሪያ ግዜ ከ1 ደቂቃ ከ58 ሰከንድ በታች ለመሮጥ የቻለች ሲሆን ያሸነፈችበት 1:57.86 የሆነ ሰዓትም የውድድር ስፍራው አዲስ ሪኮድ፣ የግሏ ምርጥ፣ እና የወቅቱ ፈጣን ሆኖ ተመዝግቧል፡፡ ወርቅነሽ መለሰ የራሷ ምርጥ በሆነ 1:59.93 ሰዓት በሁለተኛነት አጠናቃለች፡፡

ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ከአንደኛ እስከ አራተኛ ያሉትን ደረጃዎች ይዘው በጨረሱበት የሴቶች 1500 ሜትር ፍሬወይኒ ሀይሉ የራሷን ምርጥ ባሻሻለችበት እና የወቅቱ ፈጣን የሆነ 3:55.28 ሰዓት አንደኛ ወጥታለች፡፡ ፍሬወይኒ እና ድርቤ ወልተጂ እየተፈራረቁ ሲመሩ በነበሩበት ውድድር በመጨረሻ ፍሬወይኒ የአጨራረስ ፍጥነቷን ተጠቅማ ለማሸነፍ በቅታለች፡፡ ድርቤ ወልተጂ (3:55.47)፣ሒሩት መሻሻ (3:56.47)፣ እና ትግስት ግርማ (3:58.79) ሶስቱም የራሳቸውን ምርጥ ሰዓት በማሻሻል በቅደም ተከተል ከሁለተኛ እስከ አራተኛ ያሉትን ደረጃዎች ይዘው ጨርሰዋል፡፡ የመጀመሪያዎቹን ሶስት ደረጃዎች ይዘው ያጠናቀቁት ፍሬወይኒ ሃይሉ፣ ድሪቤ ወልተጂ እና ሂሩት መሸሻ ያስመዘገቡት ሰዓት በአለም የምንጊዜም ምርጥ ዝርዝር ውስጥ በሶስተኛ፣አራተኛ እና አምስተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል።

የቶሩኑ ውድድር የዘንድሮው የአለም የቤት ውስጥ ተከታታይ ውድድሮች (ወርልድ ኢንዶር ቱር) አራተኛ መዳረሻ ነበረ፡፡
