በ2026 የዳይመንድ ሊግ የፍፃሜ ውድድሮች ኢትዮጵያውያኑ ፍሬወይኒ ሀይሉ እና ገመቹ ጎዳና አሸናፊ ሆነዋል።
Ethiopia’s 2026 Diamond League champions: Freweyni Hailu (left) and Gemechu Godana (right) with their trophies. (Photo © Bizuayehu W. Yeshaw)
የ17ኛ የውድድር ዓመቱን የፍፃሜ ፉክክሮች ሴፕቴምበር 4 እና 5, 2026 በቤልጂየም ብራስልስ በማካሄድ ያጠናቀቀው የ2026ቱ ዋንዳ ዳይመንድ ሊግ በሁለቱም ፆታዎች አሸናፊ ሆነው ላጠናቀቁት አትሌቶች የዳይመንድ ሊግ ዋጫውን በመሸለም ተደምድሟል፡፡ በዓለም ዙሪያ በሚካሄዱ የአንድ ቀን የአትሌቲክስ ውድድሮች ውስጥ ዋነኛው በሆነው የዳይመንድ ሊግ ፍጻሜ የ”ዓመቱ ሻምፒዮን” የሚለውን ማዕረግ ካገኙ 32 አትሌቶች መካከል ሁለት ኢትዮጵያውያን ይገኙበታል። እነሱም የሴቶች 5000 ሜትር አሸናፊዋ ፍሬወይኒ ሀይሉ እና በወንዶች 3000 ሜትር መሰናክል ያሸነፈው ገመቹ ጎዳና ናቸው፡፡
ዓርብ ሴፕቴምበር 4/2026 – የፍፃሜ ውድድር ዕለት አንድ
የፍፃሜው ተፎካካሪ ከነበሩት አስራ አንድ አትሌቶች ስድስቱ ኢትዮጵያውያን በነበሩበት የሴቶች 5000 ሜትር ፉክክር ፍሬወይኒ ሀይሉ በድንቅ የአጨራረስ ብቃት 14:35.20 በሆነ ሰዓት አሸንፋለች፡፡ ከአንደኛ እስከ ሶስተኛ ያሉትን ደረጃዎች ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በተቆጣጠሩበት በዚህ ፉክክር ልቅና አምባው (14:36.31) እና ሰናይት ጌታቸው (14:37.09) በቅደም ተከተል ሁለተኛ እና ሶስተኛ ወጥተዋል፡፡ ፍሬወይኒ ውድድሩን በሚገባ በመቆጣጠር እና የመጨረሻውን ዙር እጅግ አስደናቂ በሆነ ፍጥነት በ59.68 ሰከንድ በመሸፈን የመጀመሪያ የዳይመንድ ሊግ የዓመቱ አሸናፊነት ድልን ተቀዳጅታለች፡፡ በዚህ ውድድር ላይ ተሳታፊ የነበሩት ሌሎች ኢትዮጵያውያን ሒሩት መሸሻ (14:37.84)፣ መዲና ኢሳ (14:39.40)፣ እና ማርታ አለማየሁ (14:40.27) በቅደም ተከተል አምስተኛ፣ ሰምንተኛ፣ እና ዘጠነኛ ሆነው ጨርሰዋል፡፡
ፍሬወይኒ ከዳይመንድ ሊጉ የፍፃሜ ድሏ በኋላ ለ BizuAthletics በሰጠችው አስተያየት “የ1500 ሜትር ሯጭ እንደመሆኔ ከ300 ወይም 400 ሜትር ተነስቼ በፍጥነት መጨረሱ ላይ ጥሩ ነኝ ብዬ ስለማምን ያንኑ ለመተግበር ተዘጋጅቼ እንደገባሁት አሳክቼዋለሁ” ብላለች።

በሴቶች የ3000 ሜትር መሰናክል ውድድር ፍፃሜ ላይ የኢትዮጵያ ብቸኛዋ ተወካይ ሆና የተሳተፈችው ኬና ቱፋ፣ ዓርብ ምሽት ብራሰልስ ላይ በተካሄደው የዳይመንድ ሊግ የፍፃሜ ውድድር 9፡12.34 በሆነ ሰዓት ሰባተኛ ደረጃን ይዛ ጨርሳለች፤ በዚህም የ2026 የውድድር ዘመኗን አጠናቃለች።
ከውድድሩ በኋላ በብራሰልስ ለBizuAthletics አስተያየቷን የሰጠችው ኬና ‹‹ባለፈው ዓመት በቪዛ ችግሮች ምክንያት በውድድሮች የመሳተፍ ብዙ እድሎች አላገኘሁም ነበር፤ በዚህ ዓመት ቪዛ ማግኘት በመቻሌ ለመጀመሪያ ጊዜ በዋና ዋና ውድድሮች ላይ በመሳተፌ እና ለዳይመንድ ሊግ ፍፃሜ ለማለፍ በመብቃቴ በጣም ደስተኛ ነኝ።›› በማለት በአለም አቀፍ መድረክ ጠቃሚ ልምድ ያገኘችበትን የውድድር ዘመን በአዎንታዊ መልኩ ገልጻዋለች።
በብራስልሱ የ2026 ዋንዳ ዳይመንድ ሊግ የመጀመሪያ ቀን ከተካሄዱት 16 የፍፃሜ ውድድሮች አፍሪካውያን አትሌቶች በአምስቱ አፍሪካውያን አትሌቶች ያሸነፉ ሲሆን ኢትዮጵያቷ ፍሬወይኒ ሀይሉም ከአምስቱ ባለድሎች አንዷ ነች፡፡
በመጀመሪያው የፍፃሜ ዕለት (ዓርብ ሴፕቴምበር 4/2026) የዋንጫ አሸናፊ የሆኑ አፍሪካውያን አትሌቶች
በወንዶች 400 ሜትር፡- ኮለን ኬቢናትሺፒ (ቦትስዋና)
በወንዶች 800 ሜትር፡- ኤማኑኤል ዋንዮኒ (ኬንያ)
በሴቶች 5000 ሜትር፡- ፍሬወይኒ ኃይሉ (ኢትዮጵያ)
በሴቶች 3000 ሜትር መሰናክል፡- ፌይዝ ቼሮቲች (ኬንያ)
በሴቶች ስሉስ ዝላይ፡- ሳሊ ሳር (ሴኔጋል)
ቅዳሜ ሴፕቴምበር 5/2026 – የፍፃሜ ውድድር ዕለት ሁለት
በብራስልሱ የ2026 ዋንዳ ዳይመንድ ሊግ ፍፃሜ የሁለተኛ ቀን ፕሮግራም ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በአራት የውድድር አይነቶች (በወንዶች 5000 ሜ፣ እና 3000 ሜ. መሰናክል፤ በሴቶች 1500 ሜ. እና 800 ሜ.) ተሳታፊ ነበሩ፡፡ በዳይመንድ ሊጉ ፍፃሜ የመጀመሪያ ቀን አፍሪካውያን አምስት የዳይመንድ ዋንጫዎችን ያሸነፉ ቢሆንም፣ ቅዳሜ ዕለት በብራሰልስ ሀገሩንም አህጉሪቱንም የሚወክል የዋንጫ ድል ያስገኘው ብቸኛ አትሌት ኢትዮጵያዊው ገመቹ ጎዳና ነበር። ገመቹ ብራስልስ ላይ በወንዶች 3000 ሜ. መሰናክል በርቀቱ እ.አ.አ. ከ2017 ዓ.ም. ጀምሮ እየተገነባ የመጣ የርቀቱ ንግስና የነበረው ሞሮኳዊው ሱፊያን ኤል ባካሊን በተከታታይ ለሁለተኛ ግዜ በማሸነፍ ጭምር ነው የዓመቱ ሻምፒዮን የሆነው፡፡ ውድድሩን 8:08.67 በሆነ ሰዓት በአንደኛነት ያጠናቀቀው ገመቹ በውድድሩ ላይ መሰናክሎቹን ያለእንከን እየዘለለ ይፈጥን የነበረበት አካሄድ ብዙዎችን ያስደነቀ ነገር ነበር፡፡ ሞሮኳዊው ሱፊያን ኤል ባካሊ (8:10.03) እና ኬንያዊው ሲሞን ኮኤች (8:11.15) በቅደም ተከተል ሁለተኛ እና ሶስተኛ ሆነው ጨርሰዋል፡፡ በዚህ ውድድር ላይ ተሳታፊ የነበረው ሌላኛው ኢትዮጵያዊ ሳሙኤል ፍሬው (8:16.51) ሰባተኛ ወጥቷል፡፡
ገመቹ ከውድድሩ በኋላ ለBizuAthletics በሰጠው አስተያየት ‹‹በውድድሩ ላይ ጥሩ አቋም ለማሳየት የሚያስችል ምቹ ከባቢ ሁኔታን ስለፈጠሩልኝ አዘጋጆቹን እና ተመልካቾቹን በጣም አመሰግናለሁ። በዳይመንድ ሊግ ውድድር ላይ ለሁለተኛ ግዜ ያውም ደግሞ በፍፃሜው ዋንጫ በማሸነፌ እና በዓለም ላይ ካሉ ምርጥ አትሌቶች ተርታ ቦታ እንዳለኝ በማረጋገጤ እጅግ ደስተኛ ነኝ›› ብሏል።

(Photo © Bizuayehu W. Yeshaw)
ኢትዮጵያዊው ቢኒያም መሐሪ ተሳታፊ በነበረበት የወንዶች 5000 ሜትር ፍፃሜ ትውልደ ኢትዮጵያዊው የባሕሬን አትሌት ብርሃኑ ባለው፣ የመጨረሻውን ዙር በ53.4 ሰከንዶች በመሸፈን በርቀቱ የወቅቱ ፈጣን እና የእስያ አህጉር አዲስ ክብረወሰን በሆነ 12፡45.70 ሰዓት አሸንፏል፡፡ ስድስት አትሌቶች ውድድሩን ከ12፡50 በታች በሆነ ሰዓት ማጠናቀቅ ችለዋል፡፡ ከእነዚህም መካከል 12፡46.73 በሆነ ሰዓት የግሉን ምርጥ ከዘጠኝ ሰከንዶች በላይ ለማሻሻል እና የአገሩን ብሔራዊ ክብረ ወሰን ለመስበር የቡሩንዲው ኤጊዴ ንታካሩቲማና ይገኝበታል፡፡ የኬንያው ኮርኔሊየስ ኬምቦይ 12፡47.29 በሆነ የግል ምርጥ ሰዓት ሶስተኛ ሲወጣ፣ ኢትዮጵያዊው ቢኒያም መሃሪ የግሉን የዓመቱ ምርጥ ባስመዘገበበት 12፡47.78 ሰዓት አራተኛ ሆኖ አጠናቋል።
ቢኒያም ከውድድሩ በኋላ ለBizuAthletics በሰጠው አጭር አስተያየት ‹‹ከምሳተፍባቸው ውድድሮች ድክመቶቼን ለማረም እና ለማሻሻል እየሞከርኩ ሲሆን በመጨረሻዎቹ ውድድሮቼ ላይም እየተሻሻልኩ መጥቻለሁ፡፡ በዛሬው ውድድር ላይ በግሌ የዓመቱን ምርጥ ሰዓቴን መሮጥ መቻሌ ጥሩ ነገር ነው›› ብሏል፡፡
ፖላንዳዊቷ አትሌት ክላውዲያ ካዚሚዬርስካ የውድድሩን እና የሀገሯ ብሔራዊ ክብረወሰን ባሻሻለችበት የወቅቱ ፈጣን የሆነ 3፡54.05 ሰዓት ቅድመ ግምቶችን ሁሉ ፉርሽ ያደረገችበት ድል ባስመዘገበችበት የሴቶች 1500 ሜትር ውድድር የተሳተፉት ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ጥሩ ምሽት አልነበራቸውም፡፡ ብርቄ ሀይሎም (4፡02.79) ዘጠነኛ ሆና ስትጨርስ ፅጌ ድጉማ በጉዳት ምክንያት ውድድሩን አቋርጣ ለመውጣት ተገዳለች፡፡
በርቀቱ በአሁኑ ግዜ ጥሩ ሰዓት እያስመገበች የምትገኘው ኢትዮጵያዊቷ ሳይዳ ፀሃዬ በሴቶች 800 ሜትር ፍፃሜ ውድድር ላይ ከስዊዘርላንዳዊቷ ኦድሬ ቬሮ (1፡54.75) እና ከኔዘርላንዳዊቷ ፌምኬ ብሮደርስ ቦል (1፡54.81) በመቀጠል 1፡57.57 በሆነ ሰዓት ሶስተኛ ሆና አጠናቃ ነበር፡፡ ሆኖም የውድድሩ አዘጋጆች በአለም አትሌቲክስ ቴክኒካል ህግ ቁጥር 17.2.3 መሰረት ከመስመር ጥሰት ጋር በተያያዘ ውጤቷ መሰረዙን አሳውቀዋል፡፡
በሁለተኛው የፍፃሜ ዕለት (ቅዳሜ ሴፕቴምበር 5/2026) የዋንጫ አሸናፊ የሆነ አፍሪካዊ አትሌት
በወንዶች 3000 ሜትር መሰናክል፡- ገመቹ ጎዳና (ኢትዮጵያ)
