በወንዶች 1500 ሜትር ለፓሪስ ኦሊምፒክ ተሳትፎ ለመብቃት ሊኬድበት የሚገባ ሌላኛው መንገድ…
ከሐምሌ 25 – ነሐሴ 5/2016 በፈረንሳይ ዋና ከተማ ፓሪስ በሚከናወነው 33ኛው የኦሎምፒክ ጨዋታዎች የአትሌቲክስ ፉክክር ላይ በወንዶች መካከለኛ ርቀት ኢትዮጵያን የሚወክሉ አትሌቶችን ለመምረጥ ሰኔ 7 ቀን 2016 በስፔን ማላጋ የመምረጫ ውድድር ለማከናወን ፕሮግራም ተይዟል። ኢትዮጵያውያን ወንድ አትሌቶች በሁለቱም ርቀቶች (በ800 ሜትር እና 1500 ሜትር) እስካሁን ለፓሪስ ኦሊምፒክ ተሳትፎ የሚያበቃቸውን ሚኒማ (ለ800 ሜትር 1፡44.70፤ ለ1500 ሜትር 3፡33̋.50 ወይም በአንድ ማይል 3፡50.40) ማስመዝገብ አልቻሉም። በመሆኑም በማላጋው የመምረጫ ውድድር ላይ የሚሳተፉ አትሌቶች ከአንደኛ እስከ ሶስተኛ ያሉትን ደረጃዎች ይዞ ከማጠናቀቅ በተጨማሪ በየርቀቶቹ የሚጠየቀውን ሚኒማ ማሟላትም ይጠበቅባቸዋል። በማላጋ በወንዶች የምርጫ ውድድር ላይ የሚሳተፉ አትሌቶች የሚፈለገውን ጊዜ (ሚኒማ) ማስመዝገብ ካልቻሉ ኢትዮጵያ በተለይ በወንዶች 1500 ሜትር አትሌቶችን ለፓሪሱ ኦሊምፒክ ልታበቃ የምትችልበትን ዕድል ቀጣዩ ጽሁፍ ለመጠቆም ይሞክራል።
‘Road to Paris 2024’ ቅድመ ፓሪስ ኦሎምፒክ የአትሌቶች ብቃት ሂደትን መከታተያ . . .
ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የዓለም አትሌቲክስ ሚኒማ አሟልተው ወይም በወርልድ ራንኪንግ በሚያስመዘግቡት ነጥብ መሰረት ለትልልቅ ውድድሮች የሚያልፉ አትሌቶችን መረጃ በይፋ የሚያሳውቅበት የመረጃ ሥርዓት ዘርግቷል። ይህ የመረጃ ስርዓት ከዋና ዋና ውድድሮች በፊት ሚኒማ ለማሟላት እና የወርልድ ራንኪንግ ነጥቦችን ለማስመዝገብ በሚቀመጡ ግዜ ገደቦች ውስጥ የሚደረጉ ውድድሮች ውጤቶችን እየተከታተለ የሚያሳውቅ ነው። በፓሪስ 2024 የኦሎምፒክ ጨዋታዎች ተሳታፊ ለመሆን የሚሞክሩ አትሌቶችን ብቃት ሂደት ለመከታተል ይረዳ ዘንድም የአለም አትሌቲክስ ‘Road to Paris 2024’ የተባለውን የኦንላይን የመረጃ ምንጭ ባለፈው ጥቅምት ወር በይፋ ስራ ማስጀመሩ ይታወቃል። የመረጃ ምንጩ በዲሲፕሊን፣ በአገር እና በብቃት ደረጃ መረጃዎችን ፈልጎ ማግኘት የሚቻልበት ሲሆን በማራቶን በሁለቱም ፆታዎች ለፓሪስ ኦሊምፒክ ተሳታፊነት የበቁ አትሌቶችን የመጨረሻ ዝርዝር ግንቦት 4/2016 አሳውቋል። በ‘Road to Paris 2024’ መረጃ መሰረት በወንዶች ማራቶን ሚኒማ በማሟላት 70፥ በዩንቨርሳል ዋይልድ ካርድ 10 በድምሩ 80 አትሌቶች፤ በሴቶች ማራቶን ደግሞ ሚኒማ በማሟላት 88፥ በዩንቨርሳል ዋይልድ ካርድ 7 በድምሩ 95 አትሌቶች ለፓሪስ ኦሊምፒክ ማራቶን ተሳታፊነት በቅተዋል። ብዙ አትሌቶች በሴቶች ማራቶን ዝቅተኛውን መስፈርት ስላሟሉ እና በወንዶች ማራቶን የተቀሩት 10 ቦታዎች ለዩኒቨርሳል ዋይልድ ካርድ ተጠቃሚዎች ስለተሰጡ በማራቶን የወርልድ ራንኪንግ ኮታ እድል የተሰጠው አትሌት የለም። የዓለም አትሌቲክስ በ100 ሜትር፣ 800ሜ እና ማራቶን ብቻ ዩኒቨርሳል ዋይልድ ካርድን የሚፈቅድ ሲሆን በነዚህ የውድድር አይነቶች ላይም ዩኒቨርሳል ዋይልድ ካርድን ከወርልድ ራንኪንግ እንደሚያስቀድም በወንዶች ማራቶን ላይ ባሳለፈው ውሳኔ አሳይቷል።
እያንዳንዱ አባል ፌዴሬሽን በአንድ የውድድር አይነት እንዲያሳትፍ የሚፈቀድለት አትሌት ብዛት 3 ብቻ እንደመሆኑ ሚኒማ ያሟሉ ከሶስት በላይ አትሌት ያላቸው ብሔራዊ ፌዴሬሽኖች በየራሳቸው የመምረጫ መስፈርቶች ሶስቱን ተሰላፊዎቻቸውን የሚለዩ ይሆናል። በ‘Road to Paris 2024’ መረጃ መሰረት በወንዶች ማራቶን ኢትዮጵያ 62 ኬንያ 77 እንዲሁም በሴቶች ማራቶን ኢትዮጵያ 98 ኬንያ 66 ሚኒማ ያሟሉ አትሌቶች ነበሯቸው። የመረጃ ምንጭ ሲስተሙ በተቀሩት የአትሌቲክስ ዲስፒሊኖች ለፓሪስ 2024 ተሳታፊነት ብቁ የሆኑ አትሌቶች/ቡድኖችን የመጨረሻ ዝርዝር ሰኔ 30/2016 ይፋ የሚያደርግ ይሆናል።
የኢትዮጵያ ወንድ አትሌቶች የ1500 ሜትር የፓሪስ ኦሊምፒክ ተሳትፎ ሌላኛው ተስፋ . . .
በወንዶች መካከለኛ ርቀት ኢትዮጵያን የሚወክሉ አትሌቶችን ለመምረጥ ሰኔ 7 ቀን 2016 በስፔን ማላጋ የሚደረገው የመምረጫ ውድድር አትሌቶቻችን የኦሊምፒክ ሚኒማውን ማሟላት የሚችሉ ከሆነ እሰየው። ካልሆነ ከላይ የተዋወቀው የመረጃ ምንጭ ‘Road to Paris 2024’ የወርልድ ራንኪንግ የነጥብ ደረጃ ኢትዮጵያውያን ወንድ የ1500 ሜትር ተወዳዳሪዎች ለፓሪስ ኦሊምፒክ ተሳታፊነት ሊበቁ የሚችሉበት ሌላኛው ተስፋ እንደሆነ ያመላክታል። በመሆኑም በተለይ በወንዶች 1500 ሜትር በፓሪስ ኦሊምፒክ ኢትዮጵያን ለመወከል ጥረት እያደረጉ የሚገኙ አትሌቶች፥ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን እና የአትሌቶቹ ማኔጅመንት ለማላጋው ውድድር ከመዘጋጀቱ ጎን ለጎን ስለሁለተኛው የማለፊያ አማራጭ ሊያስቡበት ይገባል።
በወንዶች 1500 ሜትር የኦሊምፒክ ተሳታፊ ለመሆን በቶኪዮ ኦሊምፒክ ወቅት የነበረው የመግቢያ ሚኒማ 3፡35̃̃.00 ለፓሪስ ኦሊምፒክ ወደ 3፡3.50 ዝቅ በመደረጉ በዓለም ዙሪያ ላሉ አትሌቶች ሚኒማውን ማሟላት ትንሽ ፈታኝ የሆነባቸው ይመስላል። በወንዶች 1500 ሜትር በሚኒማ እና በወርልድ ራንኪንግ ለፓሪስ ኦሊምፒክ ለማለፍ የሚያስችሉ ውጤቶችን የማስመዝገቢያ ጊዜ ከሰኔ 24/2015 – ሰኔ 23/2016 ነው። በፓሪስ 2024 የወንዶች 1500 ሜትር ውድድር ላይ እንዲሳተፉ የሚፈለገው አትሌቶች ብዛት 45 ሲሆን ይህ ፅሁፍ እስከተፃፈበት ዕለት ድረስ ሚኒማውን ያሟሉት አትሌቶች ብዛት 28 ብቻ ነው። ይህም ማለት የተቀሩት 17 ቦታዎች የሚሞሉት በወርልድ ራንኪንግ ኮታ ደረጃ ውስጥ በሚገኙ አትሌቶች ይሆናል። ይህ አሀዝ እስከ ሰኔ 23/2016 በሚኖሩ የተለያዩ ውድድሮች ላይ በሚመዘገቡ ውጤቶች ምክንያት መለዋወጡ የማይቀር ነገር ነው። እስካሁን ባለው ሁኔታ ከኢትዮጵያ ኤርሚያስ ግርማ ለፓሪስ ኦሊምፒክ ተሳትፎ ሊያበቃው በሚችል የወርልድ ራንኪንግ ኮታ ደረጃ ውስጥ ተቀምጦ የሚገኝ ሲሆን ሌሎች ሶስት አትሌቶችም (መለሰ ንብረት፥ መልኬነህ አዘዘ፥ እና ታደሰ ለሚ) በወርልድ ራንኪንግ የሚቀጥለው ምርጥ ዝርዝር ውስጥ አሉበት።
ወደ ‘Road to Paris 2024’ የደረጃ ሰንጠረዥ ለመግባት ለፓሪስ ኦሊምፒክ ብቁ ለመሆን በተቀመጠው የጊዜ ገደብ በርቀቱ አምስት ውድድሮችን ማጠናቀቅን ይጠይቃል። እስከ ሰኔ 23/2016 ድረስ በሚካሄዱ የ1500 ሜትር ውድድሮች ላይ የሚሳተፉ ከሆነ ቢኒያም መሃሪ እና ሳሙኤል ተፈራም በውጤታቸው መሰረት በወርልድ ራንኪንግ ደረጃ ውስጥ ሊገቡ የሚችሉበት ዕድል አለ።
የኢትዮጵያ የ1500 ሜትር ወንድ አትሌቶች ወርልድ ራንኪንግ ወቅታዊ ነጥብ እና ደረጃ
| የዓለም የኮታ ደረጃ | የሀገር ውስጥ ደረጃ | ሀገር | አትሌት | ሁኔታ | ዝርዝር መግለጫ |
| 43 | 1 | ኢትዮጵያ | ኤርሚያስ ግርማ | በወርልድ ራንኪንግ ኮታ ውስጥ* | በ1211ነጥብ – 55ኛ |
| 60 | 2 | ኢትዮጵያ | መለሰ ንብረት | በወርልድ ራንኪንግ የሚቀጥለው ምርጥ | በ1175 ነጥብ – 88ኛ |
| 73 | 3 | ኢትዮጵያ | መልኬነህ አዘዘ | በወርልድ ራንኪንግ የሚቀጥለው ምርጥ | በ1151 ነጥብ – 122ኛ |
| 4 | ኢትዮጵያ | ታደሰ ለሚ | በወርልድ ራንኪንግ የሚቀጥለው ምርጥ | በ1146 ነጥብ – 126ኛ |

ስለሆነም በፓሪስ ኦሊምፒክ በወንዶች 1500 ሜትር ተወዳዳሪዎችን ተሳታፊ ለማድረግ በሚደረጉ ጥረቶች ውስጥ ሚኒማውን ለማሟላት ከሚደረገው ዝግጅትና ሙከራ ጎን ለጎን የራንኪንግ ነጥባቸውን እንዲያሳድጉ ማድረግም በሁለተኛ አማራጭነት ሊሰራበት ይገባል። የ‘Road to Paris 2024’ ወርልድ ራንኪንግ ነጥብ ስሌት በሁለት ነገሮች ላይ የሚያተኩር ሲሆን እነርሱም የውድድር ውጤት (ሰዓት) እና የውድድር ውጤት ደረጃ ናቸው። በውድድር የደረጃ ውጤት የሚመዘገበው ነጥብ በሁለት ነገሮች ላይ የሚመረኮዝ ሲሆን እነርሱም በውድድሩ ላይ በሚመዘገበው ደረጃ እና ውድድሩ በዓለም አትሌቲክስ ያለው ደረጃ ናቸው። በወርልድ ራንኪንግ ከፍተኛ ነጥብ የሚመዘገብባቸው የትራክ ውድድሮች በቅደም ተከተል ዳይመንድ ሊግ፣ አህጉራዊ ሻምፒዮና፣ የወርልድ አትሌቲክስ ኮንቲኔንታል ጎልድ (ምድብ A)፣ ብሄራዊ ሻምፒዮናዎች (ምድብ B). . . እየተባሉ የተቀመጡ ሲሆን በስፔን ማላጋ የሚደረገው የኢትዯጵያ የኦሊምፒክ መምረጫ ውድድር ምድብ F ነው። የመምረጫው ውድድር አንድ አትሌት በኳሊፋዪንግ ግዜ ውስጥ ያደረጋቸውን ውድድሮች ቁጥር በመጨመሩ ረገድ የበኩሉን ሚና ከመጫወቱ ባሻገር አንደኛ ሆኖ ለሚያጠናቅቅ አትሌት 15 ነጥብ፥ ለሁለተኛ 10፥ እና ለሶስተኛ 5 ነጥብ ያስገኛል። በውድድሩ ላይ በሚኖረው ፉክክር ሚኒማውን ማሳካት ባይቻል እንኳ ወደዛ የተጠጋ ፈጣን ሰዓት ማስመዝገብም ተጨማሪ ነጥቦችን ያስገኛል።
ከዚህ ጋር በተያያዘ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ቢያንስ በየዓመቱ የሚያካሂደውን ብሔራዊ ሻምፒዮና ዓለም አቀፍ ደረጃውን በጠበቀ ኤሌክትሮኒክስ ታይሚንግ በማካሔድ አትሌቶች በወርልድ ራንኪንግ ተጨማሪ ነጥቦችን እንዲያስመዘግቡ ውጤታቸውም ዓለም አቀፍ ዕውቅና እንዲሰጠው ለማድረግ ቢሰራ መልካም ነው። በሀገር ውስጥ የሚደረጉ ውድድሮችን ፌዴሬሽኖች በዓለም አትሌቲክስ የውድድር ካላንደር ላይ አስመዝግበው ውጤት ካላስተላለፉ በስተቀር እንደከዚህ ቀደሙ በሌሎች መንገዶች ውጤቶችን መሰብሰብ ስለቆመም አትሌቶች በሀገር ውስጥ ውድድሮች ላይ የሚያስመዘግቧቸው ውጤቶች አይመዘገቡላቸውም። ይህ በተለይም አዲስ የሚመጡ አትሌቶች በሀገር ውስጥ በሚያስመዘግቡት ውጤት አማካይነት የዓለም አትሌቲክስ ድረ ገፅ ላይ ፕሮፋይል እንዳይኖራቸው እና እውቅና እንዳያገኙ የሚያደርግ ነው። ለፌዴሬሽኑም ቢሆን በሀገር ውስጥ እያከናወናቸው ያሉ ውድድሮች ውጤቶችን ዓለም አቀፍ ተደራሽነት ማሳጣት መልካም ነገር አይደለም።
በወንዶች 1500 ሜትር ሚኒማ ለማምጣት እና በወርልድ ራንኪንግ ነጥብ ለፓሪስ ኦሊምፒክ ለማለፍ የሚያስችሉ ውጤቶችን የማስመዝገቢያ ጊዜው ከሚዘጋበት ሰኔ 23/2016 በፊት የሚደረጉ የዓለም አትሌቲክስ ደረጃ A እና C እንዲሁም የአፍሪካ ሻምፒዮና ውድድሮች ያሉ እንደመሆኑ በማላጋ ሚኒማውን ማምጣት ባይቻል ተስፋ ሳይቆረጥ ያሉትን ዕድሎች በሙሉ ለመጠቀም መሞከር ነው። የወደፊት ትልቅ ተስፋ ያላቸው ወጣት አትሌቶች የትልቁን የውድድር መድረክ የኦሊምፒክ ተሞክሮ እንዲያገኙ ለማድረግ በሚቻለው መንገድ ሁሉ መሞከር ለወደፊቱ ውጤታማነታቸው መንደርደሪያ ሊሆናቸውም ይችላልና በደንብ ይታሰብበት።
