በኢትዮጵያውያን ዘንድ በጉጉት የሚጠበቀው የኦሊምፒክ አትሌቲክስ ውድድር ሐሙስ ጠዋት ይጀመራል፡፡
በፓሪስ ኦሊምፒክ በወንዶች 20 ኪሎ ሜትር እርምጃ ኢትዮጵያን ወክሎ የሚወዳደረው ምስጋና ዋቁማ (Photo © Aman Photo/ @angasurunning)
የዘንድሮው የኢትዮጵያ የኦሊምፒክ ቡድን ዝግጅት በአስተዳደራዊ የአሰራር ድክመት ትልልቅ ውድድሮች በመጡ ቁጥር የሚከሰተው አላስፈላጊ ውዝግብ ከምንግዜውም በከፋ ሁኔታ የታየበት ነው፡፡ በአለም አቀፍ የስፖርት መድረኮች የኢትዮጵያ ዋነኛ የኩራት ምንጭ በሆነው የአትሌቲክስ ስፖርት ዙሪያ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየታዩ ያሉ የአስተዳደር ድክመቶች ለስፖርቱ የወደፊት ህልውና ጠንቅ እንዳይሆኑ ያሰጋሉ። በኢትዮጵያ የአትሌቲክስ አስተዳደሪዎች እና ባለድርሻ አካላት ዙሪያ የታዘብናቸውን እየገዘፉ የመጡ ችግሮች ከኦሊምፒኩ መጠናቀቅ በኋላ ሰፋ ባለ ገንቢ ትችት እና የመፍትሔ ሀሳብ የምንመለስበት ይሆናል፡፡ አሁን በፓሪስ ኦሊምፒክ የአትሌቲክስ ውድድሮች ላይ ኢትዮጵያን ወክለው የሚወዳደሩ አትሌቶችን ማስተዋወቅ እና ከውድድሮቹ ጋር ተያያዥ የሆኑ የተለያዩ መረጃዎችን ወደእናንተ ማድረሱ ላይ እናተኩር፡፡
የኦሊምፒክ አትሌቲክስ ውድድር በኢትዮጵያውያን የስፖርቱ አፍቃሪያን ዘንድ በጉጉት የሚጠበቅ ሲሆን የፓሪስ 2024 የኦሊምፒክ አትሌቲክስ ፉክክሮችም የፊታችን ሐሙስ ጠዋት በሁለቱም ፆታዎች በሚደረጉት የ20 ኪሎ ሜትር እርምጃ ውድድሮች ይጀምራሉ፡፡ የኢትዮጵያ የፓሪስ ኦሊምፒክ የውድድር ተሳትፎም በኢትዮጵያ አቆጣጠር ሐሙስ ጠዋት 2፡30 በሚጀምረውና ምስጋና ዋቁማ በወንዶች 20 ኪሎ ሜትር እርምጃ በሚያደርገው ውድድር ይጀመራል፡፡
በወንዶች 20 ኪሎ ሜትር እርምጃ ኢትዮጵያን የሚወክለው ምስጋና ዋቁማ ማነው?
በእርሻ ሥራ የሚተዳደሩ ወላጆቹ አቶ ዋቁማ ፈቃንሳ እና ወ/ሮ ብዙነሽ ገብረማርያም ካፈሯቸው ዘጠኝ (ሰባት ወንድ እና ሁለት ሴት) ልጆች ሰባተኛው የሆነው ምስጋና ከተለያዩ ወላጆች የተገኙ ሰባት ወንድሞች እና ስምንት እህቶች አሉት፡፡ ገጠር በትምህርት ቤት እያለም ሩጫ ይሞካክር የነበረ ቢሆንም ያኔ ስፖርቱ የበዛ ትኩረት የሚሰጠው ነገር አልነበረም፡፡ ወደአዲስ አበባ ከመጣ ከስድስት ዓመት በኋላ ኮቪድ በመጣ ግዜ የስፖርት ፍቅሩ ዳግም አነሳስቶት ሩጫን ማዘውተር የጀመረ ሲሆን በዛው ቀጥሎበትም አሁን ለደረሰበት ደረጃ በቅቷል፡፡ ወደሩጫው ከመመለሱ በፊት በነበሩት ሶስት ዓመታት የሆቴል አስተናጋጅነት እና የአየር ማረፊያ ጫኝና አውራጅነትን ጨምሮ የተለያዩ ስራዎችን ሲሰራ ቆይቷል፡፡ ከገጠር ወደ አዲስ አበባ ሲመጣ ትምህርቱን አቋርጦ የነበረ ቢሆንም ወደ ዋና ከተማዋ ከመጣሁ ከሁለት ዓመት በኋላ መማር ቀጥሎ አሁን ከልምምዱ ጎን ለጎን የ11ኛ ክፍል ትምህርቱን በማታ ክፍለ ግዜ እየተከታተለ ይገኛል፡፡
ምስጋና ወደ እርምጃ ተወዳዳሪነት እንዴት እንደመጣ ሲያስረዳ ‹‹ሩጫ ስጀምር መጀመሪያ ኖርማል ሩጫ ላይ ነበረ ስሰራ የነበረው፡፡ እንዳጋጣሚ ፌደራል ማረሚያ ክለብ ለመሞከር ስሄድ ግን አሰልጣኝ ሀምሳለ ያዕቆብ ለምን እርምጃ አትሞክርም ብላ መከረቺኝ፡፡ በወቅቱ እኔ ስለ እርምጃ ምንም ስለማላውቅ ልክ እንደ 100 ሜትር ወይም 10000 ሜትር የተለየ ርቀት ነበረ የመሰለኝ፡፡ ውድድሩን ስሙን እንጂ ቴክኒኩም ምን እንደሆነ ባላውቀውም እሺ ብየ ገባሁ እና ውጤት አመጣሁኝ፡፡ የእርምጃ ሩጫ ቴክኒክን ያስተማረቺኝም አሰልጣኝ ሀምሳለ ያዕቆብ ናት፡፡ ከፌደራል ማረሚያ ክለብ ጋር ለስምንት ወር ብሰራም በአንዳንድ ሁኔታዎች ምክንያት ሊቀጥሩኝ አልቻሉም፡፡ ሌላ አማራጭ ስፈልግ እንዳጋጣሚ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ክለብን ወክዬ የአዲስ አበባ ክለቦች ሻምፒዮና ላይ ገብቼ በሶስተኛነት ሳጠናቅቅ በዛው ቀጠሩኝ፡፡ ሀገር ወክዬ በአፍሪካ ሻምፒዮና ላይ ለመሳተፍ የበቃሁትም ክለብ በገባሁበት የመጀመሪያ ዓመት ነበር›› ብሏል፡፡
የምስጋና ዋቁማ ዋና ዋና ስኬቶች
- በፓሪስ ለመጀመሪያ ግዜ በኦሊምፒክ ኢትዮጵያን ወክሎ ይሳተፋል፡፡
- ባለፈው ሚያዝያ ወር በቱርክ አንታሊያ በተከናወነው የ20 ኪ.ሜ የዓለም አትሌቲክስ የእርምጃ የቡድን ሻምፒዮና ላይ 10ኛ ሆኖ አጠናቋል።
- በ2022 ኢትዮጵያን በአዋቂዎች ውድድር ለመጀመሪያ ጊዜ በወከለበት በሞሪሸስ ሴንት ፒየር የተካሄደ የአፍሪካ አትሌቲክስ ሻምፒዮና ላይ 4ኛ ሆኖ ሲያጠናቅቅ በ2024 ያውንዴ ካሜሩን ላይ የአፍሪካ ሻምፒዮና የወርቅ ሜዳሊያ አሸናፊ ሆኗል።
- በጋና አክራ በተካሄደው የ2024 የመላው አፍሪካ ጨዋታዎች የወርቅ ሜዳሊያ አሸናፊ።
- የ2023 የአፍሪካ ከ20 ዓመት በታች ሻምፒዮና የ10,000ሜ. እርምጃ የወርቅ ሜዳሊያ አሸናፊ።
- በወቅቱ የወንዶች 20 ኪሎ ሜትር እርምጃ የዓለም ደረጃ (World Ranking) 76ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል፡፡
ምስጋና ስለወደፊት የስኬት ግቡ :- ‹‹በቴሌቪዥን የስፖርት ዘገባዎች ላይ እነ ቀነኒሳን ስመለከት እኔም እንደእነሱ ስኬታማ ሯጭ ሆኜ መቼ ነው የሀገሬን ሰንደቅ ከፍ የማደርገው የሚል ጉጉቱ ያድርብኝ ነበረ፡፡ ወደፊት በርምጃ ሩጫ በጣም ጠንክሬ በመስራት ኢትዮጵያ በማትታወቅበት በዚህ ፊልድ ከፍተኛ ውጤት ማስመዝገብ እፈልጋለሁ::››
በፓሪስ ኦሊምፒክ የወንዶች 20 ኪሎ ሜትር እርምጃ የፍፃሜ ውድድር ላይ ምን ይጠበቃል?
በአትሌቲክስ ስፖርት ከሚካሄዱት 48 የሜዳልያ ፉክክሮች የመጀመሪያው በሚሆነው የወንዶች 20 ኪ.ሜ. እርምጃ የፍፃሜ ፉክክር ላይ ጣሊያናዊው ማሲሞ ስታኖ የቶኪዮ ኦሎምፒክ አሸናፊነት ክብሩን ለማስጠበቅ ይወዳደራል። በርቀቱ የወቅቱ የአለም መሪ እና የምንጊዜም ሶስተኛ ፈጣን ሰዓት ባለቤት ጃፓናዊው ኮኪ ኢኬዳ፣ በቡዳፔስት የዓለም ሻምፒዮና ላይ በ20 ኪ.ሜ. እና 35 ኪ.ሜ. የወርቅ ሜዳልያ አሸናፊ ስፔናዊው አልቫሮ ማርቲን፣ እንዲሁም በቡዳፔስት የርቀቱ የብር ሜዳልያ እና በቱርክ አንታሊያ የተካሄደው የዓለም አትሌቲክስ የእርምጃ የቡድን ሻምፒዮና አሸናፊ ስዊድናዊው ፐርሴየስ ካርልስትሮም በፓሪስ ለሜዳልያ ደረጃዎች ብርቱ ተፎካካሪ እንደሚሆኑ ይጠበቃል፡፡
ከጉዳት አገግሞ የተመለሰው ስታኖ በፓሪስ ሌላ የኦሎምፒክ ክብረ ወሰን ስለመስበርም ያልማል። ብራዚላዊው ካይዮ ቦንፊም፣ የኢኳዶሩ ብሪያን ፒንታዶ፣ እና ቻይናዊው ዣንግ ጁን ሌሎች ጠንካራ ተፎካካሪዎች ይሆናሉ ተብለው የሚጠበቁ ተወዳዳሪዎች ናቸው፡፡
