October 29, 2026

ክፍተቶችን ከማስተባበል ይልቅ ወደፊት በሚደረጉ ውድድሮች ላይ ማስተካክል ይበጃል

በዛሬው ውድድር ላይ ምስጋና የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ የአቅሙን ሁሉ አድርጎ የነበረ ቢሆንም በውድድር ስፍራው የሚያስፈልገውን ድጋፍ ለአትሌቱ በማድረጉ በኩል የነበሩ ክፍተቶችን አስተውያለሁ፡፡ ለሁሉም ሀገራት አትሌቶች በተዘጋጀው የሚጠጡ ነገሮች ማቀበያ ቦታ ላይ ሰዎች ተመድበው አትሌቶቻቸውን የሚጠጣ በማቀበል ሲያግዙ በኢትዮጵያ ሰንደቅ አላማ ስር ከተዘጋጀው ጠረጴዛ አጠገብ ግን ሰው አልነበረም፡፡ እንደውም ቦታው ክፍት መሆኑን ያየ ፎቶግራፈር እዛ ጋር ቆሞ ፎቶ ሲያነሳበት ሁሉ ነበረ፡፡

በአይኔ እንዳየሁትም ሆነ ከአትሌቱ ጋር ከውድድሩ በኋላ በነበረኝ ቃለ ምልልስ እንዳረጋገጥኩት በመጨረሻዎቹ ጥቂት ዙሮች ላይ አሰልጣኙ አቶ ባዬ አሰፋ እና የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ባልደረባ አቶ አስፋው ዳኜ ቦታው ላይ ተገኝተው ሊያቀብሉት ከመሞከራቸው ውጪ አብዛኛውን ዙር ማንም አልነበረም፡፡ በፓሪስ ኦሊምፒክ የአትሌቲክስ ቡድን ቴክኒካል ኃላፊ አቶ ቢልልኝ መቆያ ስለጉዳዩ በክላሲክና ዳይናሚክ ስፖርት የፌስቡክ ገፅ ላይ የሰጡት ምላሽም በቀላሉ እንደስህተት ጥቆማ ተቀብሎ ለማራቶን ውድድሮቹ ማስተካከል የሚቻልን ጉዳይ በሌላ ስህተት ለማረም የሞከረ ‹‹ከዚህ ቀደም የነበረው አሰራር ተቀይሯል፡፡ ትናንት አዘጋጅ አካሎችን ውሀ የሚያቀብል ሰው እንዲፈቅዱልን ብንጠይቅም አዘጋጅ አካሉ ግን በአዲሱ አሰራር መሰረት ራሱ አትሌቱ እንዲያነሳ ተወስኗል›› የሚል ሆኗል፡፡ የሌሎች ሀገር ውሀ አቀባዮች ከየሀገራቸው ሰንደቅ ስር ከተቀመጡ ጠረጴዛዎች አጠገብ ቆመው ግዴታቸውን ሲወጡ እኛም አለምም በግልፅ ያየው ነገር ነው፡፡ ለኢትዮጵያውያን ልዑካን ብቻ የሚቀየር አሰራር እንዴት ሊኖር ይችላል?

በኦሊምፒክ ውድድሮች ላይ እንደ ጋዜጠኛ ስታደም ይህ ሶስተኛ ግዜዬ ነው፡፡ በሁሉም ተሳትፎዎቼ አትሌቶቻችን ያላቸውን አቅም ሁሉ እያወጡ ለሀገር ውጤት ለማስመዝገብ የሚያደርጓቸው ጥረቶች እና ስኬቶቻቸውም የሚያስደስተኝ ነገር ነው፡፡ ሆኖም የማስተዳደር አቅም ማነስ ወይም የበዛ ግዴለሽነት ያለባቸው የአትሌቲክስ ፌዴሬሽን እና ኦሊምፒክ ኮሚቴ ኃላፊዎች የሚፈፅሟቸው እንዲህ ያሉ ግድፈቶች ሁሌም እንዳበሳጩኝ ነው፡፡ በተለያዩ አጋጣሚዎች ስለነዚህ ችግሮች ገንቢ በሆኑ ትችቶች ስህተቶቻቸውን እንዲያርሙ ለመጠቆም ሞክሬም አውቃለሁ፡፡ ነገር ግን አሁንም አንድ አይነት ስህተቶች ተደጋግመው ሲፈፅሙ እየታዩ ይገኛል፡፡

ሌላው አትሌቶች ውድድሩ ካለቀ በኋላ በብሮድካስት እና ፕሬስ ሚክስድ ዞን ውስጥ ሲያልፉ ከዛም በኋላ የዶፒንግ ምርምራ፣ የጫማ ምዝገባ፣ እና ፕሬስ ኮንፈረንስ ማድረግን፤ ከውድድር በኋላ ልብሳቸውን መልሰው ማግኘት ሲፈልጉ የሚያግዛቸው፤ እንዲሁም ወደሆቴል ሳይጉላሉ መመለስ የሚችሉባቸውን ሁኔታ የሚያመቻች ሰው ሲጠፋም በተደጋጋሚ ታይቶ ያውቃል፡፡ ከነዚህ ጉዳዮች ጋር በተያያዘ በተለይም ውድድር ከጨረሱ በኋላ በሚክስድ ዞን አካባቢ ለሚያስፈልጋቸው እገዛ ዋነኛው ኃላፊነት የቡድኑ ፕሬስ አታሼ ተብሎ የሚመጣው ሰው ነው፡፡ ዛሬም ምስጋና ውድድሩን ከጨረሰ በኋላ ያንን የሚያደርግ ሰው ባለማየቴ የዓለም አቀፉ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ለጋዜጠኞች መረጃ ለመስጠት ባዘጋጀው አፕሊኬሽን ውስጥ ገብቼ በኢትዮጵያ በኩል የተመደበ ፕሬስ አታሼ እንዳለ ቼክ ለማድረግ ተገድጃለሁ፡፡ ባየሁት መረጃ መሰረት ሲሳይ ዮሐንስ ታሲሳ የተባለ ሰው በፕሬስ አታሼነት ስሙ ተመዝግቧል፡፡ ነገር ግን ከሚዲያ የመረጃ ፍላጎቶች ጋር በተያያዘ ከሀገር ቤትም ሆነ ከውጭ ጋዜጠኞች ፍላጎቶች እና ጥያቄዎች ቢኖሩ እርሱን ለማግኘት የሚያስችል ስልክ ቁጥርም ሆነ የኢሜይል አድራሻ የለውም፡፡ አቶ ሲሳይ ዮሐንስ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በሚወዳደሩባቸው ቦታዎች በሚገኙ ሚክስድ ዞኖች አካባቢ ያንተ እገዛ በጣም ስለሚያስፈልግ ፓሪስ ካለህ እባክህ ከዛ አካባቢ አትጥፋ፡፡ ከተለያዩ የሚድያ ፍላጎቶች ጋር የተያያዙ ጥያቄዎችን የማስተናገድ ኃላፊነትም ስላለብህ የምንፈልግህ ደውለን ወይም በኢሜይል እንድናገኝህም በፕሬስ አታሼዎች ስም ዝርዝሩ ላይ ከተቀመጠው ስምህ ጎን እባክህ ስልክ ቁጥርህን እና ኢሜይልህን አስፍርልን፡፡

ስለነዚህ ጉዳዮች የሚመለከታችሁ አካላት በመጀመሪያው የውድድር ቀን ይህን ማንሳቴ ከታዩት ክፍተቶቻችሁ ተምራችሁ በቀሪዎቹ የውድድር ቀናት ሊደረጉ የሚገባቸውን ነገሮች በተገቢው ሰዓትና ቦታ ለማድረግ እንድትሰሩ ለማስታወስ ብቻ እንደሆነ ተገንዘቡ፡፡ የእኔ ዋነኛ ትዝብትም ማን መጣ ማን ቀረ የሚለው ሳይሆን በውሀ ስቴሽን እና በፕሬስ አታሼ ቦታዎች ላይ ኃላፊነታቸውን የሚወጡ ሰዎች ያልነበሩ መሆናቸውን የሚመለከት እንደሆነ እወቁ፡፡ የውሀ ስቴሽን ጉዳይ ለማራቶን ውድድሮች የፕሬስ አታሼው ኃላፊነትን በአግባቡ የመወጣት ጉዳይም በስታድየም እና በማራቶን ውድድር ቦታዎች አስፈላጊ መሆናቸውን አትርሱ፡፡

በመጪዎቹ ቀናት ውድድራችሁን ለምታደርጉ አትሌቶች በሙሉ መልካም የውድድር እና የውጤት ግዜ ይሁንላችሁ፡፡