በቬርሳይ ዳገትና ቁልቁለት ተፈትኖ የኦሊምፒክ ወርቅ ያመጣው ታምራት ቶላ
በፓሪስ 2024 ኦሊምፒክ የወንዶች ማራቶን የሜዳልያ አሸናፊዎች (Photo Christel Saneh for World Athletics)
ሊጠናቀቅ አንድ ቀን በቀረው የፓሪስ ኦሊምፒክ በወንዶች 10 ሺህ ሜ. እና በሴቶች 800 ሜ. የብር ሜዳልያዎች ተወስና የቆየውች ኢትዮጵያ በወንዶች ማራቶን በታምራት ቶላ አማካይነት የወርቅ ሜዳልያ አስመዝግባለች፡፡ ታምራት ቶላ ለወርቅ ሜዳያ አሸናፊነት የበቃው በጣም ፈታኝ የሆነውን የቬርሳይ ዳገትና ቁልቁለት በመርታት እንዲሁም የኦሊምፒክ ሪኮርድ በመስበር ጭምር ነው፡፡ የጨረሰበት 2:06:26 ሰዓትም ኬንያዊው ሳሙኤል ዋንጂሩ በቤይጂንግ ኦሊምፒክ ላይ ያስመዘገበውን ሪኮርድ በስድስት ሰከንድ ያሻሻለ ሆኗል፡፡
በውድድሩ ላይ ወደፊት የሚወጡትን አትሌቶች ለመቆጣጠር ሲሞክር እንደቆየ የጠቀሰው ታምራት በውድድሩ ሂደት በምን አይነት ሁኔታ ውስጥ እንደነበር ሲያስረዳኝ ‹‹እውነት ለመናገር እኔ እስከ 35ኛው ኪሎ ሜትር ድረስ እወጣለሁ ብዬ አላሰብኩም ነበር፡፡ ሆኖም አንድ የጣልያን አትሌት ተነጥሎ ሲሄድ ከፊት የነበሩት እነ ኪፕቾጌ ሊይዙት ሲሞክሩ አልቻሉም ነበር፡፡ ይሄ ነገር አንዴ ካመለጠ በኋላ አስቸጋሪ ሊሆን ይችላል ብዬ ቢያንስ እሱ ላይ ላድርሳቸው እና ወደኋላ እመለሳለሁ ብዬ ነበር ወደፊት የወጣሁት፡፡ ልጁ ላይ ለመድረስ ስሄድም እነርሱ ወደኋላ ቀሩ፡፡ ከልጁ ጋር የተወሰነ እንደሄድን ሌላ አሜሪካዊ አትሌት መጣ፡፡ ከዛ በኋላም በራሴ እየሄድኩ እያለ መጥተው ሲቀላቀሉኝ አይ ይሄ ነገር በኋላ ሊከብደኝ ይችላል እናም ከግሩፑ ጋር ብሔድ ያሻላል ብዬ ከእነርሱ ጋር አብሬ መሮጥ ጀመርኩ፡፡ በመቀጠል ጃፓናዊው አትሌት ወደፊት ሲወጣ ያለው አማራጭ አሁንም መከተል ብቻ ስለሆነ እሱን ተከትዬ ወጣሁ፡፡ ከእሱ ጋር እየሄድን እያለ 29ኛው ኪሎ ሜትር አካባቢ ዳገቱ ጋር ስንደርስ እሱም አልቻለም፡፡ ዳገቱ ላይ በጣም ከብዶኝ ነበረ ነገር ግን ፈጣሪ ከረዳኝ ይሆናል ካልሆነም የሚሆነው ይሁን ብዬ ወስኜ በራሴ መሄድ የጀመርኩት ከዛ በኋላ ነው፡፡ እየራቅኩ ስሄድም ተስፋ አገኘሁ እና በዛው ቀጠልኩ፡፡ አርባ አንደኛው ኪሎ ሜትር ላይ እስክደርስ ድረስ ግን ተመልሰው ሊመጡ ይችላሉ በሚል ስጋት ስለማሸነፌ የእርግጠኝነት ስሜት አልነበረኝም›› ብሏል፡፡
ታምራት ያስመዘገበው የወርቅ ሜዳልያ ድል በኢትዮያ ቡድን ውስጥ ያለውን ስሜት ይቀይራል ብሎ ተስፋ እንደሚያደርግ ገልፆ ‹‹ኢትዮጵያ የምትታወቀው በአስር ሺህ እና አምስት ሺህ ሜትር ውጤታማነቷ ቢሆንም ዘንድሮ በእሱ እየተሳካልን ባለመሆኑ እንደማንኛውም ሰው አዝኛለሁ፡፡ ሰው ሁሉ እግዚአብሔር የሰጠውን ነገር ነው የሚያገኘው፡፡ ስራህን በአግባቡ እየሰራህ እና አሰልጣኞች የሚልሁን እየሰማህ ጉልበትህን በሚባርክልህ ፈጣሪ ተስፋ በማድረግ ሁሉም ነገር ይሳካል ብዬ አምናለሁ፡፡ ከትራክ ከወጣሁ በኋላ በጎዳና ላይ ሩጫዎች ብዙ ስኬቶችን አስመዝግቤያለሁ፡፡ በዓለም ሻምፒዮና ማራቶን ውድድር ለንደን ላይ የብር፣ ዩጂን ላይ የወርቅ ሜዳልያ ካሸነፍኩ በኋላ ቡዳፔስት ላይ አቋርጬ ነበር፡፡ አሁን ደግሞ በፓሪስ በትልቁ የኦሊምፒክ ውድድር ላይ በድል ተመልሻለሁ›› በማለት በፓሪስ ባገኘው ስኬት ከፍተኛ ደስታ እንደተሰማው አሳውቋል፡፡ በኢትዮጵያ ቡድን ውስጥ በተጠባባቂነት ተይዞ ቆይቶ ለዛሬው ውድድር 15 ቀን ሲቀረው በጉዳት ምክንያት ለመወዳደር ብቁ እንዳልሆነ ያሳወቀው ሲሳይ ለማን ተክቶ የገባው ታምራት በመጨረሻም ‹‹ይሄ ድል የኔ ብቻ ሳይሆን የሲሳይም ጭምር ነው፡፡ እግሬ ስለታመመ እሱ ቢሄድ የተሻለ ውጤት ያመጣል ብሎ ወደዚህ እንድመጣ አድርጓል፡፡ ለዚህም በጣም አመሰግነዋለሁ›› ብሏል፡፡
የዘንድሮውን ሲቪያ ማራቶን በፈጣን ሰዓት ያሸነፈው ኢትዮጵያዊው ዴሬሳ ገለታ በዛሬው ውድድር ላይ ጠንካራ ተፎካካሪ ሆኖ የታየ ሲሆን 2:07:31 በሆነ ሰዓት አምስተኛ ወጥቶ በመጀመሪያ የኦሊምፒክ ተሳትፎው የዲፕሎም ተሸላሚ መሆን ችሏል፡፡

በ5000 እና 10,000 ሜትር የሶስት ጊዜ የኦሊምፒክ እና የአምስት ጊዜ የአለም ሻምፒዮኑ ቀነኒሳ በቀለ ከመም ውድድሮች ወደጎዳና ከተሸጋገረ በኋላ ሁለት ኦሊምፒኮች ቢልፉትም ዘንድሮ ለንደን ላይ ባሳየው አስደናቂ ብቃት በፓሪስ ኦሊምፒክ ኢትዮጵያን ለመወከል በቅቷል። የማራቶን የመጀመሪያ ውድድሩን እዚሁ ፓሪስ ውስጥ ከአስር ዓመት በፊት በአሸናፊነት የጀመረው ቀነኒሳ በዛሬው ውድድር 2:12:24 በሆነ ሰዓት 39ኛ ሆኖ አጠናቋል፡፡
ቀነኒሳ ከውድድሩ በኋላ በሰጠኝ አስተያየት ‹‹በሪዮ እና ቶኪዮ የመወዳደር ዕድል ያላገኘሁ ሲሆን የፓሪሱ ውድድር ትንሽ ዘግይቶ የመጣ ይመስለኛል፡፡ ለማንኛውም በፓሪሱ ውድድር ላይ የመሳተፍ ዕድል በማግኘቴ ጥሩ ስሜት ነው ያለኝ፡፡ ኢትዮጵያ የውድድሩ አሸናፊ መሆኗም በጣም ጥሩ ነገር ነው፡፡ በግሌ ያስመዘገብኩት ውጤት ለእኔ ጥሩ ባይሆንም የወርቅ ሜዳልያ አሸናፊ በመሆናችንም በጣም ደስ ብሎኛል፡፡ አስረኛው ኪሎ ሜትር አካባቢ የጡንቻ መሳሳብ (ሀምስትሪንግ) ስለተሰማኝ ሌሎቹ አትሌቶች በሚሄዱበት ፍጥነት ለመጓዝ አስቸጋሪ ነበር፡፡ ሆኖም ውድድሩን አቋርጬ መውጣት አልፈለግኩም፡፡ የእኔ ፍላጎት የነበረው በመጀመሪያዎቹ አስር ደረጃ ውስጥ ገብቶ ማጠናቀቅ ነበረ፡፡ ያ ባይሳካም በሌላ በኩል የቡድን አጋሮቼን በማነሳሳቱ እና መደገፉ በኩል የነበረኝ ሚና እና በመጨረሻም ውጤታማ በመሆኑ ደስተኛ ነኝ›› ብሏል፡፡
አበበ ቢቂላ በ1960ው የሮም ኦሊምፒክ የዓለም አቀፍ አትሌቲክስ ድል በር ከፋች የሆነ ድልን የተጎናፀፈበት የወንዶች ማራቶን ኢትዮጵያ በኦሊምፒክ ውድድሮች ላይ መካፈል ከጀመረችበት 1956 ዓ.ም. አንስቶ ያለማቋረጥ ተወዳዳሪዎችን ስታሰልፍ ከቆየችባቸው ውድድሮች ብቸኛው ነው፡፡ በወንዶች ኦሊምፒክ ማራቶን ገዛኸኝ አበራ በሲድኒ 2000 ካስመዘገበው ድል 24 ዓመታት በኋላ ታምራት በፓሪስ ያመጣው ውጤት ኢትዮጵያ በኦሊምፒክ የወንዶች ማራቶን እስከዛሬ ያስመዘገበችውን የወርቅ ሜዳልያዎች ብዛት ወደ አምስት ከፍ ያደረገ ሆኗል፡፡ በርቀቱ የኢትዮጵያ የኦሊምፒክ ተሳትፎ ታሪክ የተመዘገበው አጠቃላይ የሜዳልያ ድልም የዛሬውን ጨምሮ 5 ወርቅ፣ 1 ብር፣ እና 3 ነሐስ ነው፡፡
በዛሬው ውድድር ለሶስተኛ ግዜ የኦሊምፒክ ሻምፒዮን በመሆን አዲስ የኦሊምፒክ ስኬት ሪኮርድ ለማስመዝገብ አልሞ የተወዳደረው ኬንያዊው ውጤታ አትሌት ኤሉድ ኪፕቾጌ በሕመም ምክንያት ውድድሩን አቋርጦ ወጥቷል፡፡ በኦሎምፒክ ማራቶን ሁለት የወርቅ ሜዳሊያዎችን ማስመዝገብ የቻሉት ሶስት ሯጮች ብቻ ሲሆኑ እነሱም ኢትዮጵያዊው አበበ ቢቂላ (በሮም 1960 እና በቶኪዮ 1964)፣ ዋልድማር ሲየርፒንስኪ ከምስራቅ ጀርመን (በሞንትሪያል 1976 እና በሞስኮ 1980)፣ እንዲሁም ኬንያዊው ኤሊዩድ ኪፕቾጌ (በሪዮ 2016 እና ቶኪዮ 2020) ናቸው።
ኢትዮጵያውያን ወንድ አትሌቶች በኦሊምፒክ ማራቶን ያስመዘገቧው የሜዳልያ ድሎች

