October 29, 2026

በ21ኛው የቲ.ሲ.ኤስ ቶሮንቶ ዋተር ፍሮንት ማራቶን ላይ ስድስት ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ይወዳደራሉ

2022 TCS Toronto Waterfront Marathon top athletes - Photo by Bizuayehu Wagaw

በኮቪድ 19 ወረርሺኝ ምክንያት ላለፉት ሶስት ዓመታት መካሄድ ያልቻለው የቶሮንቶ ዋተር ፍሮንት ማራቶን የፊታችን ዕሁድ ጥቅምት 6/2015 በአካል የሚደረግ ውድድርን ለማስተናገድ ዝግጅቱን አጠናቆ እንግዶቹን እንኳን ደህና መጣችሁ በማለት ላይ ይገኛል፡፡ በሶስት የውድድር አይነቶች ማለትም በአምስት ኪሎ ሜትር፣ ግማሽ ማራቶን፣ እና ማራቶን ወደ 22000 ተወዳዳሪዎችን በሚያሳትፈው የዘንድሮው ውድድር፣ በታዋቂ የማራቶን አትሌቶች መካከል ጠንካራ ፉክክር እንደሚታይበትም ይጠበቃል፡፡

የፊታችን እሁድ ጥቅምት 6/2015 በሚካሄደው 21ኛው የቲ.ሲ.ኤስ ቶሮንቶ ዋተር ፍሮንት ማራቶን ላይ ለመሳተፍ ስድስት ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ሐሙስ ጥቅምት 3 ቀን 2015 ቶሮንቶ የገቡ ሲሆን ዛሬ ጠዋት (አርብ ጥቅምት 4 ቀን 2015) በቶሮንቶ ኤግዚቢሽን ፕሌስ ኢነርኬር ሴንተር በተዘጋጀው የቅድመ ውድድር ጋዜጣዊ መግለጫ ላይም ታድመዋል። በውድድሩ ላይ ለመፎካከር ወደ ቶሮንቶ የመጡት ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በሴቶች የ2018 ኦታዋ ማራቶን አሸናፊዋ ገለቴ ቡርቃ፣ የ2021 የማላጋ ማራቶን አሸናፊዋ ፀጋነሽ መኮንን፣ የ2021 ፓሪስ ማራቶን አሸናፊዋ ትግስት ማሙዬ፣ እና በዳቱ ሒርጳ ሲሆኑ ከአምስት ወራት በፊት በተካሄደው የባርሴሎና ማራቶን አንደኛ እና ሶስተኛ ሆነው ያጠናቀቁት ይሁኝልኝ አዳነ እና ከበደ ዋሚ በወንዶቹ ኢትዮጵያውያን ተወካዮች ናቸው። ይሁንልኝ አዳነ የባርሴሎናውን ውድድር ያሸነፈው የግሉን ምርጥ ሰዓት እና የቦታውን ሪኮርድ በማሻሻል ጭምር ሲሆን ሶስተኛ የወጣው ከበደ ዋሚም የራሱን ምርጥ ሰዓት ወደ 2:06:03 ዝቅ ለማድረግ መቻሉ ይታወሳል፡፡

በ21ኛው የቲ.ሲ.ኤስ ቶሮንቶ ዋተር ፍሮንት ማራቶን ላይ የሚወዳደሩት ስድስት ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ከግራ ወደ ቀኝ ገለቴ ቡርቃ፣ ይሁኝልኝ አዳነ፣ ፀጋነሽ መኮንን፣ ከበደ ዋሚ፣ ትግስት ማሙዬ፣ እና በዳቱ ሒርጳ (Photo by Bizuayehu Wagaw)

የእሁዱ የታዋቂ አትሌቶች ማራቶን ውድድር ጠንካራ ኬንያውያን ተፎካካሪዎችንም አካቷል። የ2019 የቶሮንቶ ማራቶን የሴቶች ሻምፒዮን እና በካናዳ ምድር የተመዘገበው ፈጣን ሰዓት (2፡22፡16) ባለቤቷ ማግዳሊን ማሳይ፣ እንዲሁም የሀገሯ ልጅ ሩት ቼቢቶክ ከሴቶቹ መካከል የሚጠቀሱ ሲሆኑ ባርሴሊየስ ኪፕዬጎ እና ፌሊክስ ካንዲ ከሚጠቀሱት ወንዶች መካከል ይገኙበታል።

ኢትዮጵያውያን እንስት አትሌቶች የቶሮንቶ ዋተር ፍሮንት ማራቶንን ስምንት ጊዜ በማሸነፍ በበላይነት እየመሩ ይገኛሉ፡፡ በ2007 ዓ.ም. በአሻ ጊጊ አሸናፊነት የተጀመረው ስኬታማነትም በ2008 እና በ2014 በሙሉ ሰቦቃ፣ በ2009 በአማኔ ጎበና፣ በ2011 በኮረኔ ጀሊላ፣ በ2015 እና 2016 በሹሬ ደምሴ፣ እንዲሁም በ2017 በማርታ መግራ ቀጥሏል።

የቶሮንቶ ዋተር ፍሮንት አሸናፊ የሆኑ ኢትዮጵያውያን ሴት አትሌቶች ዝርዝር በቅደም ተከተል

በቶሮንቶ ዋተር ፍሮንት ማራቶን የወንዶቹ ፉክክር ኬንያውያን አትሌቶች ከፍተኛ የበላይታቸውን ያሳዩበት ሲሆን እስከዛሬ ከተካሄዱት 20 ውድድሮች 15ቱን በአሸናፊነት አጠናቀዋል። ካለፉት 20 ውድድሮች ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በወንዶቹ ፉክክር ማሸነፍ የቻሉት፤ በ2012 በሳህሌ ዋርጋ እና በ2013 በዴሬሳ ጪምሳ አማካይነት ሁለት ጊዜ ብቻ ነው።

በዘንድሮው ውድድር ላይም በታዋቂ ኢንተርናሽናል አትሌቶች መካከል ለአሸናፊነት የሚካሄደው ፉክክር በኢትዮጵያውያን እና ኬንያውያን አትሌቶች መካከል እንደሚደረግ ግልፅ ነው፡፡ ኬንያውያን ከ2014 ዓ.ም. ጀምሮ በወንዶች እያስመዘገቡት የሚገኘውን በተከታታይ የማሸነፍ የበላይነት ለማስጠበቅ፤ ኢትዮጵያውያን በሴቶች ባለፉት ሁለት ውድድሮች ላይ ያጡትን የበላይነት መልሶ ለማግኘት ብርቱ ትንቅንቅ እንደሚያደርጉ ይጠበቃል፡፡

በሁለቱም ፆታዎች ውድድሩን በአሸናፊነት ለሚያጠናቅቁ የሚሰጠው የገንዘብ ሽልማት በካናዳ ዶላር
1 ኛ – 25,000
2 ኛ – 15,000
3 ኛ – 10,000
4ኛ – 5,000
5ኛ – 3,000
6 ኛ – 2,000
የውድድር ቦታውን ሪኮርድ ለሚያሻሽሉ ተጨማሪ 15,000 የካናዳ ዶላር ይሰጣል፡፡
በሁለቱም ፆታዎች የወቅቱ የቶሮንቶ ዋተር ፍሮንት ማራቶን የውድድር ቦታው ሪኮርዶች በ2019 የተመዘገቡ ሲሆን የወንዶች በኬንያዊው ፊልሞን ሮኖ የተያዘው 2፡05፡00 እና የሴቶች በነገው ዕለትም በምትወዳደረው ኬንያዊቷ ማግዳላይን ማሳይ 2፡22፡16 ናቸው፡፡