ኢትዮጵያዊቷ እጅጋየሁ ታዬ በኪንግስተን ግራንድ ስላም ትራክ የ3000 ሜ. ውድድር አሸናፊ ሆነች፡፡
Ejigayehu Taye, Kingston Grand Slam Women's 3000m winner
በዝነኛው የቀድሞ አሜሪካዊ የአጭር ርቀት ሯጭ ማይክል ጆንሰን የተመሰረተው የፕሮፌሽናል አትሌቶች የመም ሊግ ውድድር ‹‹ግራንድ ስላም ትራክ›› ትላንት ምሽት በጃማይካ ኪንግስተን ተጀምሯል፡፡ በመክፈቻው ዕለት በተደረጉት ውድድሮች ላይ ከተሳተፉት ኢትዮጵያውያን አትሌቶች መካከልም በቻሌንጀርነት የተጋበዘችው እጅጋየሁ ታዬ የሴቶች 3000 ሜትር አሸናፊ ሆናለች፡፡

በ2025 የግራንድ ስላም ትራክ ውድድሮች ላይ ከኢትዮጵያ በሴቶች ድርቤ ወልተጂ እና ፅጌ ገብረሰላማ በወንዶች ሐጎስ ገብረሕይወት በዋና ተወዳዳሪነት (ግራንድ ስላም ሬሰር) በመፈረም፤ ከሴቶች እጅጋየሁ ዲባባ እና ከወንዶች ጥላሁን ሀይሌ ደግሞ በኪንግስተኑ የመክፈቻ ውድድር በተፎካካሪነት (ግራንድ ስላም ቻሌንጀር) የሊግ ውድድሩ መክፈቻ አካል ነበሩ፡፡
ለሶስት ቀን በሚቆየው የኪንግስተን ግራንድ ስላም ትራክ መክፈቻ ዕለት የተከናወነው የሴቶች 3000 ሜትር ኢትዮጵያዊያኑ ፅጌ ገብረሰላማ እና እጅጋየሁ ታዬ ከኬንያውያን አቻዎቻቸው ጋር ብርቱ ፉክክር ያሳዩበት ነበረ፡፡ በውድድሩ መጨረሻ ላይ የበላይነቱ ድንቅ የአጨራረስ ብቃት ባሳየችው ኢትዮጵያዊቷ እጅጋየሁ ታዬ የተወሰደ ሲሆን በአሸናፊነት ያጠናቀቀችበት 8፡28.42 የሆነ ሰዓትም የርቀቱ የሴቶች የወቅቱ የዓለም ፈጣን ሆኖ ተመዝግቧል፡፡ እጅጋየሁ አንደኛ በመውጣት 12 ነጥብ ስታስመዘግብ፣ ኬንያዊቷ አንገስ ጄቤት ንጌቲች (8፡28.75) ሁለተኛ በመሆን 8 ነጥብ፣ ኢትዮጵያዊቷ ፅጌ ገብረሰላማ በ8፡38.15 ሶስተኛ በመውጣት 6 ነጥብ አስመዝግበዋል፡፡ በኪንግስተን ግራንድ ስላም የሴቶች የረጅም ረጅም ርቀት የአጠቃላይ አሸናፊው የሚለይበት የ5000 ሜትር ውድድር የፊታችን ዕሁድ የሚካሄድ ይሆናል፡፡
በኪንግስተኑ ግራንድ ስላም የሴቶች የአጭር ረጅም ርቀት ምድብ አሜሪካዊቷ ኒኪ ሂልዝ (1፡58.23) እና ኢትዮጵያዊቷ ድርቤ ወልተጂ (1፡58.29) ብርቱ ትንቅንቅ ባደረጉበት የሴቶች 800ሜ. በቅደም ተከተል አንደኛ እና ሁለተኛ ሆነው አጠናቀዋል፡፡ የሴቶች የአጭር ረጅም ርቀት ምድብ የአጠቃላይ አሸናፊ በነገው ዕለት ምሽት ከሚደረገው የ1500 ሜትር ውድድር በኋላ የሚታወቅ ይሆናል፡፡
በኪንግስተኑ ግራንድ ስላም የመጀመሪያ ቀን የወንዶች የረጅም ረጅም ርቀት ምድብ በተካሄደ የ5000 ሜትር ፉክክር አሜሪካውያን አትሌቶች ከአንደኛ እስከ ሶስተኛ ያሉትን ደረጃዎች በመቆጣጠር አሸንፈዋል፡፡ በዚህ ውድድር ላይ ተሳታፊ የነበሩት ኢትዮጵያውያኑ ሐጎስ ገብረሕይወት (14:40.20) እና ጥላሁን ሀይሌ (14:42.20) በቅደም ተከተል አራተኛ እና ሰባተኛ ሆነው ጨርሰዋል፡፡ የወንዶች የረጅም ረጅም ርቀት የአጠቃላይ አሸናፊው የሚለይበት የ3000 ሜትር ውድድር የፊታችን ዕሁድ ምሽት የሚከናወን ይሆናል፡፡
‹‹ግራንድ ስላም ትራክ›› የዓለም ፈጣን አትሌቶችን በየዓመቱ ከሚያዝያ እስከ ሰኔ በሚደረጉ አራት የመም ላይ የሊግ ውድድሮች (slams) ላይ በማፎካከር ዳጎስ ያለ የገንዘብ ሽልማት የሚሰጥ አዲስ ውድድር ነው፡፡ አዘጋጆቹ በ2025 ዓ.ም. የመጀመሪያ ዓመት ውድድራቸውን በጃማይካ ኪንግስተን፤ እንዲሁም በዩናይትድ ስቴትስ ሚያሚ፣ ፊላደልፊያ፣ እና ሎስ አንጀለስ ከተሞች ለማከናወን ፕሮግራም አውጥተው የመክፈቻ ውድድራቸውን ትላንት በጃማይካዋ ዋና ከተማ ኪንግሰተን አሀዱ ብለዋል፡፡ በዚህ ውድድር ላይ አትሌቶች በስድስት የውድድር አይነቶች ማለትም በስፕሪንት፣ መሰናክል እና የርቀት ሩጫዎች ይፎካከራሉ። የሊግ ውድድሩ ለወንዶች እና ለሴቶች የተዘጋጁ ስድስት የፉክክር ምድቦች ያሉት ሲሆን እያንዳንዱ ምድብም ሁለት የውድድር ዓይነቶችን ያካትታል፡፡ በአንድ ውድድር ላይ ስምንት አትሌቶች የሚፎካከሩ ሲሆን አራቱ ‹‹ግራንድ ስላም ሬሰርስ›› በሁሉም የሊግ ውድድሮች (slams) ላይ በቋሚነት የሚሳተፉ ይሆናል፡፡ ለተሳትፎ የሚመረጡት ተጨማሪ አራት አትሌቶች ‹‹ግራንድ ስላም ቻሌንጀርስ›› ደግሞ ብቃታቸውን ለማሳየት እና በሚቀጥለው የውድድር ዘመን ቦታ ለማግኘት ይፎካከራሉ። በያንዳንዱ የግራንድ ስላም ሁለት ፉክክሮች ድምር ውጤት በነጥብ ከአንደኛ እስከ ስምንተኛ ያሉትን ደረጃዎች ይዘው የሚጨርሱ አትሌቶችም በደረጃቸው ቅደም ተከተል መሰረት ከ100 ሺህ እስከ 10 ሺህ የአሜሪካን ዶላር የገንዘብ ሽልማት የሚያገኙ ይሆናል፡፡ ለአጠቃላይ ውድድሮቹ ለሽልማትነት የተመደበው አጠቃላይ የገንዘብ መጠን 12.6 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ነው፡፡ በነጥብ ፉክክሩ በድምር ውጤት እኩል የሚመጡ አትሌቶች ካሉ አሸናፊው በተጨማሪ የመለያ መስፈርቶች (tie-breakers) የሚለይ ይሆናል።
የግራንድ ስላም ትራክ ውድድሮች የሁለቱም ፆታዎች የፉክክር ምድቦች
| የውድድር አይነት | የመጀመሪያ ውድድር | ሁለተኛ ውድድር |
| አጭር ስፕሪንት | 100 m | 200 ሜ. |
| አጭር መሰናክል | 100 ሜ. መሰናክል (ሴት) 110 ሜ. መሰናክል (ወንድ) |
100 ሜ. |
| ረጅም ስፕሪንት | 200 ሜ. | 400 ሜ. |
| ረጅም መሰናክል | 400 ሜ. መሰናክል | 400 ሜ. |
| የአጭር ረጅም ርቀት | 800 ሜ. | 1500 ሜ. |
| የረጅም ረጅም ርቀት | 3000 ሜ. | 5000 ሜ. |
