እጅጋየሁ ታዬ እና ድርቤ ወልተጂ የኪንግስተን “ስላም ሻምፒዮን” ሆኑ
2025 Kingston Slam Champions Ejgayehu & Diribe
በኪንግስተን ግራንድ ስላም ትራክ ውድድር የመጨረሻ ቀን ኢትዮጵያውያኑ እጅጋየሁ ታዬ እና ሀጎስ ገብረህይወት በ5000ሜ እና በ3000ሜ. አሸንፈዋል፡፡
ላለፉት ሶስት ቀናት በጃማይካ ዋና ከተማ ኪንግስተን አስተናጋጅነት የተካሄደው የ2025 ዓ.ም. የመጀመሪያው የግራንድ ስላም ትራክ ውድድር ዛሬ ሲጠናቀቅ በሴቶች የረጅም ረጅም ርቀት ምድብ እጅጋየሁ ታዬ የ5000 ሜትር ፉክክሩን 14:54.88 በሆነ ሰዓት በአንደኛነት አጠናቃለች፡፡ በተጋባዥ ተፎካካሪነት (ግራንድ ስላም ቻሌንጀርነት) በኪንግስተን የተገኘችው እጅጋየሁ በምድቡ በ3000 ሜትር እና 5000 ሜትር ያደረገቻቸውን ሁለቱንም ውድድሮች በቀዳሚነት በማጠናቀቅ በ24 ነጥብ የ‹‹ስላም ሻምፒዮን›› ለመሆን በቅታለች፡፡ በዚሁ ምድብ ዋና ተወዳዳሪ (ግራንድ ስላም ሬሰር) በመሆን የተፎካከረችው ኢትዮጵያዊቷ ፅጌ ገብረሰላማ የ5000 ሜትር ውድድሩን 15:24.62 በሆነ ሰዓት በሶስተኛነት አጠናቃለች፡፡ በ3000 ሜትር ውድድሩ ላይም በተመሳሳይ የሶስተኛ ደረጃን ይዛ አጠናቃ የነበረችው ፅጌ በድምሩ 12 ነጥብ በማስመዝገብ የአጠቃላይ ውድድሩንም በሶስተኛነት ለማጠናቀቅ እና የ30,000 ዶላር ተሸላሚ ለመሆን ችላለች፡፡
በወንዶች የረጅም ረጅም ርቀት ምድብ በተካሄደው የ3000 ሜትር ውድድር ላይ በ5000 ሜትር ውድድሩ በአሜሪካውያኑ አትሌቶች የተቀደመበት አካሄድ እንዳይደገም የፈለገው ሐጎስ ገብረሕይወት ወደፊት ቀድሞ በመውጣት ብቻውን መርቶ 7:51.55 በሆነ ሰዓት አሸንፏል፡፡ ውድድሩ እንደተጀመረ የሀገሩ ልጅ ሐጎስን አስከትሎ ወደፊት ወጥቶ የነበረው እና በኋላም ከሌሎቹ ተወዳዳሪዎች በሰፊ ርቀት ቀድሞ ሐጎስን ሲከተል የቆየው ጥላሁን ሀይሌ 8:00.68 በሆነ ሰዓት ሁለተኛ ሆኖ ጨርሷል፡፡ የዚህ ምድብ የነጥብ አጠቃላይ አሸናፊነት የ5000 ሜትር አሸናፊ በነበረው እና በ3000 ሜትር ሶስተኛ ሆኖ በጨረሰው አሜሪካዊው ግራንት ፊሸር (18 ነጥብ) ሲወሰድ ሐጎስ ገብረሕይወት በ17 ነጥብ ሁለተኛ በመሆን የ50,000 ዶላር ተሸላሚ ሆኗል፡፡ በ10 ነጥብ አራተኛ ሆኖ ያጠናቀቀው ጥላሁን ሀይሌም የ25,000 ዶላር ተሸላሚ ለመሆን በቅቷል፡፡ ሐጎስ ገብረሕይወት ዘንድሮ ከኢትዮጵያ የግራንድ ስላም ትራክ ዋና ተወዳዳሪ (ግራንድ ስላም ሬሰር) ሆኖ እየተሳተፈ ያለ ብቸኛው ወንድ አትሌት ሲሆን ጥላሁን ሀይሌ በኪንግስተን የተገኘው በተጋባዥ ተፎካካሪነት (ግራንድ ስላም ቻሌንጀርነት) ነው፡፡
ከኢትዮጵያ በዘንድሮው የግራንድ ስላም ትራክ ዋና ተወዳዳሪ (ግራንድ ስላም ሬሰር) ከሆኑት ሁለት ሴት አትሌቶች አንዷ የሆነችው ድርቤ ወልተጂ ሌላኛዋ የ‹‹ስላም ሻምፒዮን›› ለመሆን የበቃች አትሌት ሆናለች፡፡ በሴቶች የአጭር ረጅም ርቀት ምድብ የተፎካከረችው ድርቤ በመጀመሪያው ቀን በ800 ሜትር ሁለተኛ እንዲሁም በሁለተኛው ቀን በ1500 ሜትር አንደኛ በመውጣት በድምሩ ባስመዘገበችው 20 ነጥብ የ100,000 ዶላር ሽልማቱ አሸናፊ ሆናለች፡፡
የመክፈቻው የግራንድ ስላም ትራክ የውድድር ዓመት ሁለተኛ መዳረሻ የሚሆነው ማያሚ ስላም በሚራማር፣ ፍሎሪዳ በሚገኘው አንሲን የስፖርት ኮምፕሌክስ ሜይ 2፣ 3 እና 4፣ 2025 የሚካሄድ ይሆናል።
በግራንድ ስላም ትራክ ኢቨንት በእያንዳንዱ አስተናጋጅ ከተማ በሚደረግ ውድድር ላይ የሚሳተፉት አትሌቶች በሚያደርጓቸው ሁለት ውድድሮች በሚያስመዘግቡት ድምር ነጥብ እና ደረጃ መሰረት የሚያገኙት የሽልማት ገንዘብ መጠን፡-
1ኛ 100,000 ዶላር
2ኛ 50,000 ዶላር
3ኛ 30,000 ዶላር
4ኛ 25,000 ዶላር
5ኛ 20,000 ዶላር
6ኛ 15,000 ዶላር
7ኛ 12,500 ዶላር
8ኛ 10,000 ዶላር
