October 28, 2026

የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ለኮፐንሃገን 2026 የዓለም አትሌቲክስ የጎዳና ላይ ሩጫ ሻምፒዮና የተመረጡ አትሌቶችን ይፋ አደረገ።

የዓለም አትሌቲክስ የጎዳና ላይ ሩጫ ሻምፒዮና መስከረም 9 እና 10 ቀን 2019 ዓ.ም. በዴንማርክ ኮፐንሃገን ይካሄዳል። የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽንም በዚህ ውድድር ላይ ኢትዮጵያን ወክለው እንዲወዳደሩ የተመረጡ አትሌቶችን ስም ዝርዝር በዛሬው ዕለት (ሐምሌ 21 ቀን 2018 ዓ.ም.) ይፋ አድርጓል፡፡

ፌዴሬሽኑ የአትሌቶችን ስም ዝርዝር ይፋ ባደረገበት እና ጥሪውን ባስተላለፈበት ማስታወቂያ በሁለቱም ፆታዎች በግማሽ ማራቶን፣ በአምስት ኪሎ ሜትር፣ እና በአንድ ማይል የተመረጡትን ከነተጠባባቂዎቹ አሳውቋል፡፡ በተሰላፊነት እና በተጠባባቂነት የተያዙ አትሌቶች በሙሉም ማስታወቂያው ከተነገረበት ቀን ጀምሮ ባሉት ተከታታይ ሶስት ቀኖች ውስጥ በፌዴሬሽኑ ፅሕፈት ቤት ተገኝታችሁ በአስቸኳይ ሪፖርት እንድታደርጉም ተብሏል፡፡ በምርጫው ላይ ቅሬታ ያላቸው አትሌቶች ካሉ ማስታወቂያው ከወጣበት ቀን ጀምሮ ባሉት ተከታታይ ሶስት ቀኖች ውስጥ ለፌዴሬሽኑ ፅሕፈት ቤት ቅሬታቸውን ማቅረብ እንደሚችሉ ተገልጿል፡፡

የዓለም አትሌቲክስ የጎዳና ላይ ሩጫ ሻምፒዮና (ቀደም ሲል የዓለም አትሌቲክስ የግማሽ ማራቶን ሻምፒዮና በመባል ይታወቅ የነበረው) በዓለም አትሌቲክስ የሚዘጋጅ እና በየሁለት ዓመቱ የሚካሄድ ዓለም አቀፍ የጎዳና ላይ ሩጫ ውድድር ነው። እ.ኤ.አ. በ1992 ዓ.ም. የተመሰረተው ይህ ውድድር፣ በ2006 ወደ 20 ኪሎ ሜትር ሩጫ ለአጭር ጊዜ ተቀይሮ የነበረውን ጨምሮ በርካታ የስም እና የቅርፅ ለውጦችን አድርጓል። ውድድሩ በ2007 ዓ.ም. ወደ ግማሽ ማራቶን ርቀት የተመለሰ ሲሆን፣ አሁን ያለውን የዓለም አትሌቲክስ የጎዳና ላይ ሩጫ ሻምፒዮና የሚል ስያሜም በ2020 አግኝቷል።

በኮፐንሃገን ለ26ኛ ግዜ የሚከናወነው ይህ ዓለም አቀፍ ሻምፒዮና የቅርብ ጊዜ ውድድሩ የተካሄደው በ2023 በላቲቪያ ሪጋ ነበር። ውድድሩ ግዜውን ጠብቆ ከሁለት ዓመት በኋላ በዩናይትድ ስቴትስ ሳን ዲዬጎ እንዲካሄድ ለሴፕቴምበር 2025 ፕሮግራም ተይዞለት የነበረ ቢሆንም ለአስፈላጊ እቅድ እና ዝግጅት የሚሆን በቅ ጊዜ ባለመኖሩ በሚል ምክንያት ሳይካሄድ ቀርቷል፡፡

ኢትዮጵያ ይህ ሻምፒዮና ከተጀመረ አንስቶ በተካሄዱት በሁሉም ውድድሮች ላይ ተሳታፊ ነበረች፡፡ በምንግዜም የሜዳልያ ሰንጠረዡ ላይም በ15 የወርቅ፣ 24 የብር፣ እና 20 የነሐስ በድምሩ በ59 ሜዳልያዎች ከኬንያ ቀጥላ በሁለተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣ ትገኛለች፡፡