በኦሪገን በሚካሄደው የዓለም አትሌቲክስ ከ20 ዓመት በታች ሻምፒዮና ኢትዮጵያ በ16 አትሌቶች ትወከላለች፡፡
በሴቶች 400ሜትር የወቅቱ የአፍሪካ ሻምፒዮን እና በኦሪገን 26 ኢትዮጵያን ከሚወክሉት አትሌቶች አንዷ የሆነችው አጃይባ አልዬ
ከሐምሌ 29 – ነሐሴ 3/2018 ዓ.ም. (እ.ኤ.አ. ከኦገስት 5 እስከ 9/2026) በዩናይትድ ስቴስ ኦፍ አሜሪካ ዩጂን ኦሪጎን ሄይዋርድ ፊልድ በሚካሄደው የዓለም አትሌቲክስ ከ20 ዓመት በታች የአትሌቲክስ ሻምፒዮና ላይ ኢትዮጵያ በ11 ሴቶች እና 5 ወንዶች አትሌቶች ትወከላለች፡፡
የዓለም አትሌቲክስ ዛሬ (ሐምሌ 24 ቀን 2018) ይፋ ባደረገው የተሳታፊ አትሌቶች ስም ዝርዝር መሰረት ከ147 አባል ፌዴሬሽኖች የተውጣጡ ከ1800 በላይ አትሌቶች ለመወዳደር እንደተመዘገቡ አሳውቋል። ይህም የዓለም ከ20 ዓመት በታች አትሌቲክስ ሻምፒዮና 40ኛ ዓመቱን እያከበረ ባለበት ወቅት በውድድሩ ታሪክ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸውን ተሳታፊ አትሌቶች ለማስተናገድ እየተዘጋጀ እንዳለ የሚጠቁም ነው። የቀደመው ከፍተኛ የተሳታፊ አትሌቶች ቁጥር በ2024 በሊማ ፔሩ የተመዘገበው 1558 ነበር።
በዚህ የዓለም ከ20 ዓመት በታች የአትሌቲክስ ሻምፒዮና ላይ የኢትዮጵያ አትሌቶች በወንዶች 800 ሜትር፣ 1500 ሜትር፣ 5000 ሜትር፣ እና እርምጃ፤ በሴቶች 400 ሜትር፣ 800 ሜትር፣ 1500 ሜትር፣ 3000 ሜትር፣ 5000 ሜትር፣ እና 3000 ሜትር መሰናክል ውድድሮች ላይ እንደሚሳተፉ የዓለም አትሌቲክስ ያወጣው መረጃ ይጠቁማል።

