ትላንት ምሽት በኖርዌይ ኦስሎ በተከናወነው የዳይመንድ ሊግ 5000 ሜ. ውድድር ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በወንዶችም በሴቶችም ከአንደኛ እስከ ሶስተኛ ያሉትን ደረጃዎች በመቆጣጠር አሸንፈዋል፡፡
በዝናባማ የአየር ሁኔታ ውስጥ በተካሄደው የሴቶች 5000 ሜትር ፉክክር ዳዊት ስዩም በመጨረሻዎቹ መቶ ሜትሮች ውስጥ ፍጥነቷን በመጨመር ጉዳፍ እና ለተሰንበትን ቀድማ አንደኛ ወጥታለች፡፡ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ለኦሪገን 2022 የአለም ሻምፒዮና ከመረጣቸው ዕጩ አትሌቶች ዝርዝር ውስጥ ያልተካተተችው ዳዊት በኦስሎ ያሸነፈችበት 14፡25.84 የሆነ ሰአት የራሷ ምርጥ ሲሆን እጅጋየሁ ታዬ (14.12.98) እና ለተሰንበት (14፡24.59) ባለፈው ወር በዩጂን ካስመዘገቧቸው በመቀጠልም የዘንድሮ የአለም ሶስተኛው ፈጣን ነው፡፡ በውድድሩ ላይ ከነበሩት ሌሎች ኢትዮጵያውያን መካከል በዘንድሮው የውድድር ዓመት በርቀቱ የመጀመሪያ ተሳትፎዋን ያደረገችው አልማዝ አያና በ14:32.17 ስድስተኛ ሆና አጠናቃለች፡፡ ሀዊ ፈይሳ በ14:33.66፣ ፅጌ ገብረሰላማ በ14:43.90፣ እና አበራሽ ምንሴዎ በ14:47.98 በቅደም ተከተል ሰባተኛ፣ አስረኛ እና አስራ አንደኛ ሆነው ሲያጠናቅቁ ሶስቱም ያስመዘገቡት ሰዓት የራሳቸውን ምርጥ ያሻሻሉበት ሆኗል፡፡ ጥሩነሽ ዲባባ እ.ኤ.አ. በጁን 2008 ዓ.ም. ያስመዘገበችውና 14:11.15 የሆነው የኦስሎ ዳይመንድ ሊግ የሴቶች 5000 ሜትር የውድድር ስፍራ ሪከርድ ይሰበራል ተብሎ ተጠብቆ የነበረ ቢሆንም ሳይሳካ ቀርቷል፡፡
ዳዊት ስዩም ውድድሩን በድል ካጠናቀቀች በኋላ ለውድድሩ አዘጋጆች በሰጠችው አስተያየት ‹‹ዛሬ ለእኔ ደስታን ስላመጣልኝ በውድድሩ ሰዓት የነበረውን ዝናብ ወድጄዋለሁ ማለት እችላለሁ፡፡ ጠንካራ ተፎካካሪዎች የነበሩበት ከባድ ውድድር ነበር እናም ሁሉንም ለማሸነፍ በቅቻለሁ። በርቀቱ የራሴን ምርጥ ሰዓት ማሻሻል መቻሌም አስፈላጊ ነበር፡፡ በስታድየሙ ውስጥ በከፍተኛ ስሜት ድጋፍ ይሰጡን የነበሩ ወገኖቻችን ነበሩ። ለሰጡን ድጋፍ እናመሰግናለን።›› ብላለች፡፡
በኦስሎ የወንዶች 5000 ሜትር የመጨረሻ ፉክክሩ በኢትዮጵያውያኑ ጥላሁን ሀይሌ እና ሳሙኤል ተፈራ መካከል የነበረ ሲሆን ጥላሁን የ1500 ሜትር ስፔሻሊስቱ ሳሙኤልን በአጨራረስ ፍጥነት ቀድሞ በ13:03.51 በአንደኛነት አጠናቋል፡፡ ሳሙኤል ተፈራ የራሱ ምርጥ በሆነ 13:04.35 ሁለተኛ ሲወጣ ጌትነት ዋለ የግሉ የዓመቱ ምርጥ በሆነ 13:04.48 ሶስተኛ ደረጃን ይዞ ጨርሷል። በውድድሩ ላይ የነበሩት ሌሎች ኢትዮጵያውያን ሚልኬሳ መንገሻ በ13:05.94 አምስተኛ እንዲሁም አሊ አብዱልመናን የራሱ ምርጥ በሆነ 13:16.97 አስረኛ ወጥተዋል፡፡
ጥላሁን ሀይሌ ውድድሩን በአሸናፊነት ካጠናቀቀ በኋላ ለውድድሩ አዘጋጆች በሰጠው አስተያየት ‹‹ሶስት ኢትዮጵያውያን የመጀመሪያዎቹን ሶስት ደረጃዎች ይዘን መጨረስ መቻላችን ጥሩ አፈጻጸም ነበር። እየጠነከርኩ እንደሆነ የተሰማኝ ሲሆን በውድድሩ እና ባስመዘገብኩት ሰዓትም ተደስቻለሁ። ለረጅም ጊዜ ጉዳት ላይ ስለነበኩ ወደ አሸናፊነቱ መመለስ መቻሌ በጣም ጥሩ ነው።›› ብሏል፡፡
በኦስሎ የሴቶች 800ሜ. ውድድር ላይ ተፎካካሪ የነበረችው ኢትዮጵያዊቷ ድሪቤ ወልቴጂ በ1፡58.69 አምስተኛ ሆና አጠናቃለች።